ዜና ዜና

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የመስኖ ግብርናን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገለፀ።

በአገሪቷ የሚካሄደውን የመስኖ ግብርና ለማሳደግ የሚያስችል ሰፊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የዓለም ባንክ ገልጿል።

የዓለም ባንክ የአፍሪካ ቀጠና ምክትል ፕሬዝዳንት ሃፌዝ ጋኔም በኢትዮዽያ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ።

ምክትል ፕረዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የዓለም ባንክ በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር የሚያከናውናቸውን የትብብር ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል።

በተለይም በመስኖ ግብርና ማስፋፋት፣ በትምህርት ዘርፍና በዲጂታል ኢኮኖሚ የተጠናከረ ስራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረው ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በተለይም የመስኖ ግብርናን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማገዝ ባንኩ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግስት የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎችና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥረቶችን እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ለባንኩ ስትራቴጂክ አገር በመሆኗ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ የገለጹት ሃፌዝ ጋኔም፤ ባለፈው ሳምንት የምክትል ፕሬዚዳንትነት ሹመት ከተሰጣቸው ወዲህ የመጀመሪያ የስራ ጉብኝታቸውን በአገሪቷ ማድረጋቸው የስትራቴጂካዊ ግንኙነቱ ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል።

 አዲስ አበባ ሰኔ 3/2010(ኢዜአ)