ዜና ዜና

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ገበያ ያቀረበችው የግምጃ ቤት ሰነድ (ቦንድ) የሚሸጥበት የገንዘብ መጠን ጭማሪ አሳይቷል

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ገበያ ያቀረበችው የግምጃ ቤት ሰነድ (ቦንድ) የሚሸጥበት የገንዘብ መጠን በአስር ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ።

የግምጃ ቤት ሰነድ (ቦንድ) አንድ መንግሥት ወይም ተቋም ለብድር መተማመኛ ዋስትና የሚሆን ሕጋዊ ዶክመንት አዘጋጅቶ ብድሩን ለሚሰጠው ወገን የሚያቀርበው ነው።

ሰነዱ ውስጥ የብድርና የወለድ መጠን እንዲሁም ብድሩ ተጠቃሎ የሚመለስበት ቀንና ዋናውን ብድር ጨምሮ ከወለዱ ጋር መልሶ የሚከፈለውን ገንዘብ ያካተተ ነው።

የቦንድ ሽያጭ በዋናነት የፋይናንስ እጥረትን ለመፍታት የሚከናወን ሲሆን በገበያው ላይ ዋነኛ ተዋናዮች የሚባሉት የአገሮች መንግሥታት፣ ተቋማት፣ ኮርፖሬቶችና ሰዎች ቤት ለመግዛት የሚወስዱትን ብድር የሚያበድሩ ባንኮች (ሞርጌጅ ባንኮች) ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የቦንድ ገበያ በ2007 ዓ.ም ተቀላቅላ በዓለም አቀፍ ገበያ ቦንድ መሸጥ መጀመሯ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ገበያ ያቀረበችው የግምጃ ቤት ሰነድ የሚሸጥበት የገንዘብ መጠን በአስር ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ ማሳየቱን ሮይተርስ በድረ ገጹ አስፍሯል።

አንድ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ቦንድ ይሸጥ ከነበረበት 0 ነጥብ 583 ሳንቲም ወደ 100 ነጥብ 25 ዶላር ከፍ ማለቱን በአሜሪካ የኢኮኖሚ ቁጥራዊ አሀዞችን በመተንተን መረጃዎችን የሚያቀርበው ቶምሰን ሮይተርስ አስታውቋል።

በተለይም ከሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የአንዱ ቦንድ ሽያጭ በየቀኑ የሶስት ዶላር ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ኢንቨስተሮች በተወሰነ መልኩ ቢሆን የአገሪቱ ቦንድ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና እንዲገዙ እያደረገ መሆኑን በኬንያ የሚገኘው ስታናቢክ ባንክ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ተንታኝ ጂብራን ኩርዬሺ ለሮይተርስ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ የቦንድ ገበያ ተቋማት ትንተና መሰረት ኢትዮጵያ እዳዋና በአገሪቱ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዕዳዋን የመክፈል አቅም አይተው የB+ (Fairly good) ደረጃ ሰጥተዋት በጥሩ ሁኔታ ላይ የምትገኝ አገር ተብላለች።

በቦንድ ሽያጩ አማካይነት በየጊዜው ይበደራል ማለት አለመሆኑንና አስፈላጊ ሲሆን ብቻ ሽያጩን በድጋሚ በማከናወን ብድር ማግኘት እንደሚቻል መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ነበር።

በቦንድ ሽያጭ የሚገኘው ብድር ለኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ፣ ለኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታና ለተወሰኑ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ እንደሚውልም መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል።

በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ ሽያጩ ያገኘውን ብድር ላይከፍልባቸው ይችላል በሚል ከተቀመጡት ሀሳቦች መካከል ከኤርትራ ጋር ጦርነት ይከሰታል የሚል የነበረ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ ያደረጉትን ጉብኝት ሁኔታውን ቀይሮታል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የቦንድ ገበያ መጠን ከ100 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መድረሱን የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ውስጥ አሜሪካ 33 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚ ስትሆን ጃፓን 14 በመቶ ድርሻ ይዛ ትከተላታለች።

ሐምሌ 2/2010/አዜአ/