ዜና ዜና

እናቶች የወሊድ ፍቃዳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በየመስሪያ ቤታቸው ለልጆቻቸው የጡት ወተት የሚያቆዩበት አሰራር ሊጀመር ነው

እናቶች የወሊድ ፍቃዳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በየመስሪያ ቤታቸው ሆነው ለልጆቻቸው የጡት ወተት የሚያቆዩበት አሰራር በመዲናዋ በሚገኙ ልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች ሊጀመር ነው ተባለ።

ቅዱስ ጳዉሎስ ሚሊኒየም ኮሌጅ ሆስፒታል ከካናዳ መንግስት ጋር ይፋ ያደረገው ፕሮጀክት በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በይፋ የሚጀመር መሆኑ ገልጿል።

በሆስፒታሉ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል የስነ-ተዋልዶ ባለሙያ ዶክተር እውነት ገብረ ሀና ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አንደገለጹት አሰራሩ እናቶች የወሊድ ፍቃዳቸዉን እስከ አራት ወራት ድረስ ባለው ጊዜ ሲያጠናቅቁ ለማጥባት የሚመከረውን ተጨማሪ ሁለት ወራት በሚሰሩበት ቦታ ሆነው ለልጆቻቸው ወተቱን በማለብ የሚያቆዩበት ዘዴ ነው።

ይህም ህጻኑ አስፈላጊውን የእናት ጡት ወተት ሳይቆራረጥ እንዲያገኝ እና ጤናማ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
ለዚሁ ሲባልም የእናት ጡት ወተቱን ማቀዝቀዣ ፍሪጅ ማለቢያ ቁስ አቀዝቅዞ ማጓጓዣ የመሰሉ ነገሮች ጥቅም ላይ ይውላሉ በየመስሪያ ቤቶችም ለእናቲቱ የተከለለ ቦታ መዘጋጀት ይኖርበታል ተብሏል።

ይህ አሰራር በአራት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገበት ይገኛል።

ፕሮጀክቱ በቅዱስ ጳዉሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል ግራንድ ቻሌንጅ ካናዳ ከተሰኘ የካናዳ መንግስት በተገኘ የ97 ሺህ የካናዳ ዶላር የሚካሄድ ነው ተብሏል።

በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ውጤት ካሳየ በተለያዩ አካባቢዎች ማዳረስ እንዲቻል እስከ አንድ ሚሊዮን የካናዳ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑም ተገልጿል፡

ሐምሌ 2፣ 2010 (ኤፍቢሲ)