ዜና ዜና

የተለያዩ ሀገራት የመስቀል አደባባዩን የቦምብ ጥቃት እያወገዙ ነው

የተለያዩ ሀገራት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ እና እውቅና ለመስጠት በአዲስ አበባ በተጠራው ሰልፍ ላይ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት አወገዙ።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በቅዳሜው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በመኮነን፥ ህይዎታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

በአደጋው ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶችም በእርሳቸውና በደቡብ አፍሪካውያን ስም መጽናናትን ተመኝተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሃገሪቱ የጀመሩትን የለውጥ ጉዞ ሃገራቸው እንደምትደግፍም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ኢራን በቅዳሜው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዛለች።

የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባህራም ቃሴሚ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ የተፈጸመውን ጥቃት ቴህራን በጽኑ ታወግዛለች ብለዋል።

የተፈጸመው ጥቃት በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት እንደሌለው ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ ጉዳት ለደረሰባቸውና ሰለባ ለሆኑ ዜጎች በሃገራቸው መንግስትና ህዝብ ስም ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን በማምጣት ዴሞክራሲን ለማስፈን እያደረጉት ላለው የለውጥ ጉዞም ኢራን ሙሉ ድጋፏን ታደርጋለችም ነው ያሉት።

ሰኔ 18 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)