ዜና ዜና

የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት አዲስ አበባ ይገባል

የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት አዲስ አበባ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባሳለፍነው ሳምንት በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነጋገር የሀገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ማሰባቸውን መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ ነው የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ ልዑኩን በዚህ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ የሚልከው።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮ- ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በመገምገም፥ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ለመተግበር መስማማቷን መግለጹ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)