ዜና ዜና

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረው ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ድል እንዲጠናከር ተጠየቀ

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተጀመሩ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲያ ድል የተገኘበት ፕሮጀክት በመሆኑ ሕዝባዊ ተሳትፎው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለፀ።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ዓለም አቀፍ ግንኙነት አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከክፍለ ከተሞች የተውጣጡ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ትናነት ተካሂዷል።

በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የወሰን ተሻጋሪ ውሃዎች አማካሪ ተፈራ በየነ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዓለም አቀፉን የውሃ ሕግና አሰራር የተከተለና ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ያጠናከረ ፕሮጀክት ነው።

ድንበር ተሻጋሪ ውሃዎችን በተመለከተ በመንግስታቱ ድርጅት በ1997 ከጸደቁ አስገዳጅ ዓለም ዓቀፉ የውሃ ድንጋጌዎች መካከል የአገሮች የውሃ ሀብት አጠቃቀም ፍትሃዊና ምክንያታዊ፣ በሌሎች ላይ ጉልህ ተጽዕኖ የማያሳድር፣ መረጃ መለዋወጥና የግንባታ ዕቅዶችን ማሳወቅ፣ ተፋሰስ መጠበቅና መንከባከብ የሚሉትን አካተዋል።

በዓለም አቀፉ ድንጋጌ ዕይታ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያለችው ግድብ በናይል ተፋሰስ ከተገነቡ በርካታ ግድቦች በተለየ ሁኔታ ዓለም አቀፉን የውሃ አጠቃቀም ሕግ የተከተለ መሆኑን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት ሌላ ተፈጥሯዊ የኃይል አማራጭ እንደሌላት ገልጸው፤ ተፈጥሯዊ የውሃ ሃብቷን ለመጠቀም መጀመሯ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቅምን መሰረት ለማድረጓ ጉልህ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ አገሮች የውሃ ግድቦች ደህንነትና ዘላቂ የውሃ አቅርቦት የሚያረጋግጥ እንደሆነም ተናግረዋል።

ግንባታው ከተጀመረ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው ግድቡ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ የሕዝቦች ተሳትፎ እንዲረጋገጥ፣ የቁጠባ ባህል እንዲዳብር፣ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትና ተፈጥሮ ሀብት አጠቃቅም እንዲረጋገጥ ያስቻለ ነው።

ከዚም ባሻገር ግድቡ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በተፋሰሱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲጎለበት አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።

የግድቡ ግንባታ በብዙ መልኩ የአገሪቱን የውጭ ግንኙነት እያሳደገ መሆኑን አቶ ተፈራ ገልጸው፤ "ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታሪክ በናይል ወንዝ ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ዕድል የከፈተ ፕሮጀክት ነው" ብለዋል።

ግድቡ የቴክኖሎጂና ዕወቀት ሽግግር ዘርፍ ከሚጫወተው ሚና ባሻገር፤ ወደፊትም በተለይም የዘርፉ ተቋማትና ልሂቃን በህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ዘርፍ የውጭ ግንኙነት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ከተማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘውዱ ገብረኪዳን በበኩላቸው፤ "ፕሮጀክቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ሳይጎዳ የአገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር ነው" ብለዋል።

በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ በመገንባት ላይ የሚገኘው ግድቡ፤ የኢትዮጵያን አቅም ያገናዘበና ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት ለግድቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት ወይዘሮ ዘውዱ፤ ወደፊትም የአብሮነት ምልክት የሆነው ግድብ ለፍጻሜ እስኪበቃ ድረስ ድጋፋቸውንና የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሁን ላይ 65 በመቶው የደረሰ ሲሆን እስካሁን 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ተመልክቷል።

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010/ኢዜአ