ዜና ዜና

የኬሚካል ግብዓት፣ የበጀት እና ሌሎች የተግባር ትምህርቱን የሚፈታተኑ ችግሮችን ይፈታል ያለውን ቴክኖሎጅ ማበልፀጉን የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር አስታውቋል።

መማሪያ ላቦራቶሪን ተክቶ ሳይንሳዊ ሙከራዎችን መስራት የሚያስችል ቴክኖሎጅ የማበልጸግ ስራ ማጠናቀቁንየሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  ገለጸ።

ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ መሰናዶ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት በቤተ ሙከራ የታገዘ እንዲሆን ቢደረግም፥ የባለሙያ፣ የግብዓት እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራበት አለመሆኑን ተማሪዎች ይናገራሉ።

የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የኬሚካል ግብዓት፣ የበጀት እና ሌሎች የተግባር ትምህርቱን የሚፈታተኑ ችግሮችን ይፈታል ያለውን ቴክኖሎጅ ማበልፀጉን አስታውቋል።

ቴክኖሎጅው በሁሉም የሀገሪቱ 2ኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሚደረግና የኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ እና ሂሳብ ትምህርቶችን፥ በቁሳዊ ላቦራቶሪ ከሚሰጠው በተሻለ መልኩ በሶፍትዌር በመታገዝ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ቴክኖሎጅው ከትምህርት ስርዓቱ ጋር የተጣጣመ እና ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑን የማረጋገጥ ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ቴክኖሎጅው ለኬሚካል እና ሌሎች ግብዓቶች የሚወጣውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከማስቀረት ባለፈ፥ ከዚህ ቀደም በተግባር ለማሳየት የሚያዳግቱ የተግባር ትምህርቶችን ለማሳየት የሚጠቅም መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ሀገር ውስጥ በሚገኙ የሶፍትዌር አልሚ ጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች ለተዘጋጀው ቴክኖሎጅራ፥ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

ከትምህርት ስርዓቱ ጋር በተጣጣመ መልኩ ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ የተነገረለትን ቤተ ሙከራ፥ በዚህ አመት መጨረሻ ለትምህርት ሚኒስቴር የማስረከብ ስራ ይሰራልም ብለዋል ሚኒስትሩ።

በመጭው አመትም ቴክኖሎጅውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገው ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን።

የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ስለተባለው ነገርም ሆነ ስለ ጉዳዩ ምንም መረጃ እንደሌለው ገልጿል።

በሚኒስቴሩ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው አሰራሩም ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ትምህርት ሚኒስቴር ቴክኖሎጅው ሊኖረው ከሚችለው ጥቅም አንጻር ቢቀበልም፥ በሚቀጥለው አመት ተግባራዊ ለማድረግ ግን አስቸጋሪ ይሆናል ነው ያሉት።
ከዚህ አንጻርም በባለሙያዎች ዳግም የሚጠና መሆኑን ዳሬክተሩ አንስተዋል።

አቶ እሸቱ ይህን ይበሉ እንጅ ቴክኖሎጅው ሲዘጋጅ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ የተመከረበት መሆኑን፥ ጣቢያችን ከሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

   አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 11 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)