ዜና ዜና

ዘመን ባንክ የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዢ ፈፀመ፡፡

ዘመን ባንክ ለሁለተኛ ጊዜ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የአንድ ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ፈፀመ።

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቦንድ ግዥና ርክክብ በተደረገበት ወቅት የዘመን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ዘበነ እንደተናገሩት ባንኩ ከዚህ በፊትም የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዢ ፈፅሟል።

የባንኩ ሰራተኞችም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለቦንድ ግዢ ማበርከታቸውን ገልፀው፤ አሁንም ባንኩ በድጋሚ የቦንድ ግዢ መፈፀሙን ተናግረዋል።

የግድቡ መገንባት ሀገሪቷ ከበለፀጉ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጉዞ የሚደግፍ መሆኑን ገልፀው፤ "ግድቡ በራሳችን አቅም የእድገት ተምሳሌት ሆነን ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት አመላካች ነው" ብለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ በበኩላቸው ባንኩ ከዚህ በፊትም ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዢ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

"የፋይናንስ ተቋማት ለግድቡ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ ነው" ያሉት አቶ ታገል፤ ዘመን ባንክ ለሁለተኛ ጊዜ ቦንድ በመግዛት አርአያ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባንኩን በአርአያነት በመከተል ባለሃብቶችና በፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ቦንድ በመግዛት የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩና ለመጪው ትውልድ መልካም ታሪክ እንዲያስቀሩም ጠይቀዋል።

ሁሉም ኀብረተሰብ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተካሄዱ ሁነቶችና ፕሮግራሞች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉ ይታወቃል።

 አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010(ኢዜአ)