ዜና ዜና

በደቡብ ክልል የወረዳና ዞን አደረጃጀትን መልሶ ለማዋቀር ጥናት ተጀምሯል – አቶ ሽፈራው ሽጉጤ

በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚነሱ የአስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የወረዳዎችንና ዞኖችን በአዲስ መልክ ለማዋቀር ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የደኢህዴን ሊቀመንበር ሽፈራው ሽጉጤ ገለፁ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ለአምስት ቀናት የከፍተኛ አመራሮች ኮንፈረንስ አካሂዷል።
ኮንፈረንሱን አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ ሽፈራው እንደተናገሩት፤ የኮንፈረንሱ ዋና ዋና አጀንዳዎች ባለፉት ወራት የተደረጉ የድርጅቱ የለውጥ እንቅስቃሴዎችና በማህበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ የተሰሩ ሥራዎች መገምገም ነበር።

በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለው የወረዳና የዞን መዋቅር በ1998 ዓ ም የክልሉ ህዝብ 14 ሚሊዮን ብቻ በነበረበት የተደራጀ በመሆኑ የሚነሳውን የአስተዳደር ጥያቄ በጥናት የተደገፈ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከክልሉ ህዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የዞንና የወረዳ አስተዳደራዊ መዋቅር ለማከናወን የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ መወሰኑን አስታውሰዋል።
በዚሁ ውሳኔ መሰረት አንዳንድ ወረዳዎችንና ዞኖችን መልሶ ለማዋቀር የተጀመረው ጥናት በጥንቃቄ በሚካሄድበት ሁኔታ ላይ በተካሄደው ኮንፈረንስ በስፋት የተመከረበት መሆኑን አቶ ሽፈራው አስረድተዋል።

በትንሽ ልዩነት ላይ በመመስረት እየተከፋፈሉ በመሄድ የተበታተነ ኃይል እንዳይፈጠር ለመከላከል በመደማመጥና በመወያየት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ዕድል የፈጠረ መድረክ እንደነበረም ገልጸዋል።
በአባላት ምልመላ፣ አመራር ምደባና ማሰናበት አሰራር ድርጅቱ ያለበትን ደረጃ በመገምገም ጉድለትና ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ምስራቅ ጉጂና በጌዲዮ ዞን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ያጋጠመውን የዜጎች መፈናቀል ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልል መንግስትና ኦህዴድ ጋር በቅንጅት እየተሰራና የችግሩ መነሻ ምንጭ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በዛሬው ዕለትም በስፍራው ግጭቶች አሉ" ያሉት አቶ ሽፈራው ችግሩን ለመፍታትና ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የተፈናቃዮች ቁጥር ሰፊ በመሆኑ ከኢህአዴግ፣ ከፌዴራልና ከክልሉ አስተዳደርና መሪ ድርጅት ጋር በመሆን በመግባባት እተሰራ መሆኑን በመግለፅ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችም እንዳሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ተወላጆች በሌሎች አካባቢዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነም አቶ ሽፈራው ተናግረዋል።
ድርጅቱ በክልሉ እና በአገር አቀፍ ደረጃ የዜጎች የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ዕንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ ሥራ ለመስራት መግባባት ላይ እንደተደረሰ ጠቁመዋል።
በክልሉ የሚገኙ የሌሎች ብሔር ተወላጆች በእኩልነት እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተካሄደው ኮንፈረንሰስ በፌዴራልና በክልሉ የሚገኙ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችና የወረዳና የዞን ቁልፍ አመራሮች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010 (ኢዜአ)