ዜና ዜና

ገበያን በማረጋጋት ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ተሸለሙ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ገበያን በማረጋጋትና የአባላትን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ግንባር ቀደም  ሚና  የተጫወቱ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች እውቅናና ሽልማት ተበረከተላቸው።

ሽልማቱና እውቅናው የግብርና ምርቶችን ለማቀነባበር የሚያደርጉትን ጥረት ለማሳካት ብርታት እንደሚፈጥርላቸው የተለያዩ ክልል ተሸላሚዎች ተናግረዋል።

"የህብረት ስራ ማህበራት ምርትና አገልግሎት ውጤታማነት ለዘላቂ ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለት ቀናት በድሬዳዋ የተካሄደው 10ኛው አገር አቀፍ የኅብረት ስራ ማህበራት ቀን በዓል ትናንት ተጠናቋል፡፡

በበዓሉ ማጠናቀቂያ ላይ በተካሄደው የሽልማቱ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የፌዴራል ኅብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማር ስሩር እንደተናገሩት ማህበራቱ የአባሎቻቸውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት ቁመና ላይ እየደረሱ ነው፡፡

ድህነትን ለመቀነስና ህጋዊነትን ለማረጋገጥ፣ የግብይት ድርሻቸውን ለማሳደግ፣ የዜጎች የቁጠባ ባህልን ለማዳበርና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

በተለይ በአገሪቱ በሚከናወኑ ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የአባላቱ ፍትሃዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም ከ14 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባን ያሰባሰቡ፣ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ከ84ሺ የሚበልጡ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖችን ማፍራት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ለእውቅናና ለሽልማት የበቁት የህብረት ስራ ማህበራት በቀጣይ በተለያዩ የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ውስጥ በመሳተፍ ለአገሪቱ የምጣኔ ሐብታዊ ሽግግር  አስተዋጽዎ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አቶ ኡስማን አክለው ገልጸዋል።

የእለቱ ተሸላሚዎችም በቁጠባ፣ በብድር፣ በኢንቨስትመንት፣ አባላትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ በማድረግ እና በኦዲት ክዋኔ ግንባር ቀደም ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው፡፡

ለተሸላሚ ማህበራት፣ ዩኒየንና ፌዴሬሽን የተዘጋጀላቸውን የእውቅና የምስክር ወረቀትና የላብ ቶፕ ሽልማት የሰጡት የግብርናና እንስሳት ሐብት ልማት ሚኒስትር ድኤታ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ናቸው።

ከተሸላሚዎቹ መካከል የአዲስ አበባ ብሩህ ተስፋ ዩኒየን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለምሰገድ መክብብ "ሽልማቱ በቀጣይ ያሰብነውን የግብርና ምርት ማቀነባበር ፕሮጀክት ለማሳካት የሚያነሳሳ ነው" ብለዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የተሸለመው የጨርጨር ኦዳ ቡልቱም የገበሬዎች የህብረት ስራ ዩኒየን ኃላፊ አቶ ንጉሴ ለገሰ በበኩላቸው "ሽልማቱ በዩኒየኑ ስር ላሉ 132 መሰረታዊ ማህበራትና ለ43ሺ አባል አርሶ አደሮች ቀጣይ ስራ ልዩ መነቃቃት የሚፈጥር ነው" ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ በ49 ሚሊዮን ብር ቡናን ፈጭቶና አሽጎ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለማሳካት ሽልማቱ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በሽልማቱ በክልል ደረጃ ኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ ክልሎችም ተቋዳሽ ናቸው፡፡

 ድሬዳዋ ሰኔ 5/2010 (ኢዜአ)