ዜና ዜና

ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን – የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች

ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ከ1 ሚሊዮን 150 ሺህ ብር በላይ በቦንድ ግዥ ድጋፍ መደረጉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የከተማው  ነዋሪና በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ኪዳኔ ኃይሌ ለኢዜአ እንዳሉት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በራሳቸው ስም 70 ሺህ ብር ከወለድ ነፃ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ አድርገዋል።

ለራሳቸው ከገዙት በተጨማሪ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው በጥቅሉ የ80 ሺህ ብር ቦንድ ገዝተው መሸለማቸውንና ልጆቻቸውም በሀገር ልማት እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ የግድቡ ፕሮጀክት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ግልጸዋል።

የግድቡ ፕሮጀክት በአገሪቱ በየዘርፉ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ፋይዳው የጎላ መሆኑን በመረዳታቸው ግንባታው አስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በመጪው   አዲስ አመት የመጀመሪያ ወር የ70 ሺህ ብር ቦንድ ዳግም ለመግዛት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ በጉልት የችርቻሮ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ጡርዬ ጌታቸው በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሚኖረውን አገራዊ ፋይዳ በተለያዩ መድረኮች  መስማታቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በልማት  ቡድናቸው  አማካኝነት ለግድቡ ግንባታ የ200 ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውንና በቀጣይም ይህን ለማጠናከር  ከልማት ቡድኑ አባላት ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድነት ያነሳሳ ታላቅ አገራዊ ፕሮጀከት ነው ያሉት ወይዘሪት ሺብሬ አለሙ የተባለች የከተማዋ ነዋሪዎች ናቸው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ከ1 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጓን አስታውሳ ዘንድሮም  " ስለ ዓባይ እሮጣለሁ " በሚል በተካሄደ ንቅናቄ  የ500 ብር ቦንድ መግዛቷንና በቀጣይም ድጋፏን አጠናክራ ለመቀጠል ማቀዷን ተናግራለች።

የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወቀ ዘነበ በበኩላቸው እንዳሉት የደብረ ብርሀን ከተማ ጨምሮ የዞኑ ነዋሪዎች ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ በዚህ ዓመት ብቻ 1 ሚሊዮን 150ሺህ ብር በቦንድ ግዥ ድጋፍ  አድርገዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በቅርቡ ስላአባይ እሮጣሁ በሚል መሪ ቃል በተካሄደ የጎዳና ላይ እሩጫም በካናቲራ ግዥ 639 ሺህ 400 ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች የግድቡ ግንባታ ለሕዝብ ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ የዘንድሮን ሳይጨምር  ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና ልገሳ ድጋፍ ማድረጋቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሸን ጉዳዮች መምሪያ የተገኘውን መረጃ ያመለክታል።

አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010/ኢዜአ/