ዜና ዜና

የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ለማሳካት በቅንጅት እንደሚሰሩ የኦህዴድ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

በኮፈንፈረንሱ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን በመተግበር የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ለማሳካት  በቅንጅት እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የኦህዴድ ስምንተኛው  ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ።

ኮንፍረንሱ በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ  አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ልማትን ለማስቀጠልና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለማረጋገጥ እየተደረጉ ባሉት እንቅስቃሴዎች የተገኙ ጅምር ውጤቶችን  ለማጠናከር የሚያስችላቸውን ግብዓት እንዳገኙበትም ተናግረዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የአርሲ ዞን የፖለቲካና የገጠር አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አደም ቡሼ እንዳሉት ኮንፍረንሱ በድርጅትና በመንግስት በየደረጃው የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት የማስፈጸሚያ ስልቶችና ውሳኔዎች የሚቀመጡበት ነው።

ህብረተሰቡ እያነሳ ያለውን ሁሉን አቀፍ የለውጥ፣የፍትህና ዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ለመመለስ የድርጅቱን ውስጣዊ አሰራር የሚፈትኑ ችግርች ለመፍታት አጋዥ የሆኑ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት  ልዩ መድረክ እንደሆነም አመልክተዋል።

"የህዝቡን የለውጥና የሽግግር ጉዞን እውን ለማድረግ በኮንፈረንሱ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን  ለመተግበር ራሳችን ያዘጋጀንበት ነው"  ብለዋል።

የለውጥ እንቅስቃሴውን ለማደናቀፍ እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች ለማክሰም ህዝብን ከጎን በማሰለፍ ርብርብ  እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

በክልሉም ሆነ በሀገሪቷ እየተመዘገቡ ያሉ ጅምር ድሎች ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት በየቦታው የሚታዩ ችግርች ያኮረፉ አካላት አፍራሽ ሴራ መሆኑም ጠቁመዋል።

"ይህን እንቅስቃሴ ለማስወገድ የድርጅቱን አባላት፣ወጣቶች፣ሴቶችና መላውን ህብረተሰብ በባላቤትነት ባሳተፈ መልኩ ለመረባረብ ቃላችንን ዳግም የምናድስበት ነው "ብለዋል።

ኮንፈረንሱ የድርጅቱ ውስጣዊ ጥንካሬዎችና ክፍተቶች በውል የተለዩበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከምዕራብ ሐራርጌ ዞን ሐዊ ጉዲና ወረዳ የተወከሉት አቶ ኢንዲሪስ ኢብራሂም ናቸው።

የህዝቡን የሰላም፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ህብረተሰቡን በባለቤትነት ለማሳተፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በየቦታው የሚታዩት ጥቃቅን ችግሮች ግለኝነትና ኪራይ ሰብሳቢነት የተጠናወታቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የፈጠሩት አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምዕራብ ሐራርጌ ዞን የከተሞች አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ታጁዲን ሙሓመድ  በበኩላቸው ኮንፍረንሱ  በጥልቅ ተሃድሶ የተገኙትን ድሎችና አሁን ያለውን መነቃቀት በማጣመር ለተሻለ ለውጥ ለማምጣት  ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ድርጅቱ ራሱን በትክክል የፈተሸበትና የለውጡ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ስጋቶችን የተለየበት መድረክ መሆኑን አመልክተዋል።

" ጅምር ድሎችን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ቀዳሚ አጀንዳችን አድርገን የወሰድነው የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ማሳካትና ሽግግሩን ማፋጠን ነው "ብለዋል።

በዚህም ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑ ግንባር ቀደም የድርጅቱ አባላት ተመርጠው ወደ አመራር እንዲመጡ መደረጉን ጠቅሰዋል።

እርምጃው ድርጅቱ በየጊዜው ራሱን እየፈተሸና እየገነባ ለህዝቡ ሁሉን አቀፍ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተገነዘቡበት መድረክ እንደሆነም አመልክተዋል።

በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አደራሽ ትናንት የተጀመረው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ 8ኛ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ  እንደቀጠለ ነው።

 

  አዳማ ሰኔ 4/2010(ኢዜአ)