ዜና ዜና

በትጥቅ ትግል ሲሳተፉ የቆዩ የኦነግ አመራሮች ወደ አገራቸው ተመለሱ

የቀድሞ የኦህዴድ መስራችና የሥራ አስፈጻሚ የነበሩ አቶ ዮናታን ዱቢሳና የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩት ኮሎኔል አበበ ገረሱ የትጥቅ ትግላቸውን በመተውና በተፈጠረው ሰላም ተጠቅመው አስተዋጽኦ ለማድረግ ወደ አገራቸው ተመለሱ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አብይ አህመድ ያደረጉትን የሰላምና የፍቅር ጥሪ ተቀብለው ሁለቱ በትጥቅ ትግል ሲመሩና ሲሳተፉ የነበሩ ሰዎች ተመልሰዋል።

አቶ ዮናታን አገራቸውን ለቀው ከወጡ በኋላ ተቀማጭነታቸውን ኤርትራ በማድረግ በኦነግ ውስጥ የፖለቲካ ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ ነበር።
ከአስራ ሰባት ዓመት በላይ ከአገራቸው ወጥተው የተመለሱት አቶ ዮናታን እንደሚሉት፤ አሁን ያለው የተረጋጋ ፖለቲካ ሁኔታ በመፈጠሩ ወደ አገራቸው ለመመለስ ወስነው ተግባራዊ አድርገውታል።

"የቀረቡት ሰላማዊ ጥሪዎች በሙሉ አርኪና ሳቢ በመሆናቸው በአገር ውስጥ በተፈጠረው ሁኔታ ዕድል በመገኘቱ ለመመለስ ወስኛለሁ" ብለዋል።
ኮሎኔል አበበ ገረሱ ቀደም ሲል የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩና አንድ መቶ የሰራዊቱን አባላት በመያዝ ወደ ኦነግ በመቀላቀል ሲዋጉ መቆየታቸው ነው የተወሳው።

ከኢትዮጵያ ከወጡ ከ11 ዓመት በላይ የሆናቸው ኮሎኔል አበበ እንዳሉት፤ በአገር ውስጥ በሰላም መቃወምና ሁሉም የሚፈልገውን መስራት የሚችልበት ሁኔታ በመፈጠሩና ሰላማዊ ጥሪ በመደረጉ ለመመለስ ወስነዋል።

"ልማት እየተስፋፋ ለመኖር የሚቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ጥሪውን ተቀብለን መጥተናል" ሲሉ ነው የገለጹት።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በሰጡት ማብራሪያ ሰዎቹ ወደ አገራቸው የተመለሱት "በፍቅር ጦርነት ተሸንፈው " ሲሉ ነው የገለጹት።
ሁኔታውን ልዩ የሚያደርገው ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር መሆኑንም ገልጸዋል።

ካይሮ ሰኔ 4/2010(ኢዜአ)