ዜና ዜና

በጋሞ ጎፋ ዞን በደን ልማት የተሰማሩ አርሶአደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ፡፡

 

በጋሞ ጎፋ ዞን በደን ልማት የተሰማሩ አርሶአደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ፡፡

በዞኑ 55 ሺህ 212 አርሶ አደሮች ከእርሻ ስራ በተጓዳኝ በደን ልማት መሰማራታቸውን የዞኑ አካባቢ ጥበቃና ደን ጽህፈት ቤት ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ገዜ ጎፋ ወረዳ የዳዳ ገሃ ወይራ ቀበሌ አርሶ አደር ሱላ ሹሬ በሰጡት አስተያየት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ጽድ ተክለው በማልማት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ካለሙት ጽድ ላይ የተወሰነውን ለገበያ በማቅረብ ዘንድሮ ከ35 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሚያካሂዱት የእርሻና የእንስሳት ሀብት ልማት በተጨማሪ በደን ልማት መሰማራታቸው ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ኑሮአቸው እንዲለወጥ እያገዛቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለሽያጭ የደረሰውን ዛፍ ሲቆርጡ ሌላ ችግኝ እንደሚተክሉ የገለፁት አርሶ አደሩ በዚህም ከዘርፉ የሚያገኙት ገቢ እንደማይቋረጥ ተናግረዋል፡፡

በቦንኬ ወረዳ የገረሰ ዛላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መንግስቱ ደበበ በበኩላቸው ለእርሻ ስራ በማይመች ማሳቸው ላይ ባህር ዛፍ በማልማት ዘንድሮ 30 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

ከደን ልማት በተጨማሪ ችግኝ አፍልተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የወረዳው አስተዳደርና ደን ልማት ጽህፈት ቤትም ከሚያለሙት ደን ተገቢውን ገቢ እንዲያገኙ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን አከባቢ ጥበቃና ደን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ኩማ በበኩላቸው በገደላማና ተዳፋት መሬቶች ላይ የሚለማው ደን የአርሶ አደሮች ኑሮ እየተለወጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በዞኑ 55 ሺህ 212 አርሶ አደሮች ከ3 ሺህ 816 ሄክታር በላይ ደን ማልማታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአርሶ አደር ማሳ የሚከናወነው የደን ልማት ለአየር ንብረት ከሚሰጠው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በቀጣይ ይኸው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን 19 ነጥብ 82 የነበረው የዞኑ የደን ሽፋን አሁን 24 ነጥብ 62 መድረሱን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 አርባምንጭ ግንቦት 30/2010 (ኢዜአ)