ዜና ዜና

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለሕዳሴው ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለሕዳሴው ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ።

የሕዳሴው ግድብ የሰላም ዋንጫ ትላንት ጅማ ከተማ ሲደርስ በከተማው ነዋሪዎች፣ በምዕራብ ዕዝ 4ኛ ሬጅመንትና በኦሮሚያ ፖሊስ ሠራዊት አባላት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

የ4ኛ ሬጅመንት ተወካይ ኮሎኔል ሰይፉ አብይ የሰላም ዋንጫውን ከ5ኛ ሬጅመንት በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረጉ አገራዊ ጥረቶች የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በመሆኑም መላው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከሚያደርጉት ሙያዊ ግዴታ ባሻገር ለግድቡ እውን መሆን ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የሰላም ዋንጫው በምዕረብ ዕዝ በሚገኙ ክፈለጦሮችና ሬጅመንቶች እንደሚዘዋወር አመልክተው የሠራዊቱ አበላት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።

ኮሎኔል ሰይፉ እንዳሉት የታለቁ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የሰራዊቱ አባላት በየዓመቱ በአንድ ወር ደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት ድጋፍ  ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የ12ኛ ክፍለጦር ምክትል አዛዥና የሰው ሀብት ልማት ኃላፊ ኮማንደር ምሩጽ ወልደሚካኤል በበኩላቸው መላው የሠራዊቱ አባላት ላለፉት ሰባት ዓመታት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የሰላም ዋንጫው በየአካባቢያቸው በሚዘዋወርበት ወቅትም የሠራዊቱ አባላት ከፍተኛ አክብሮት በመስጠት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የገለጹት።

በሰላም ዋንጫ ርክክብ ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የጅማ ከተማ አፈጉባኤ አቶ ሰለሞን ቀኖ በበኩላቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ መግባባትንና አንድነትን ማጠናከር የቻለ የልማት ምሰሶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወደጅማ ከተማ የሰላም ዋንጫው መምጣትን አስመልክተው የ100 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ በመፈጸም ለገድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማው ባለሀብት ወይዘሮ ፋሲካ ገብሬ ናቸው።

ሻምበል ሽብሬ ዲምቲ የተባሉ የሰራዊቱ አባል በበኩላቸው በበዛሬው ዕለት የ100 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውንና በቀጣይም መላ ቤተሰባቸውን የሕዳሴው ግድብ ወደሚገነባበት ሥፍራ በመውሰድ ለማስጎብኘት ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡

የሕዳሴው ግድብ የሰላም ዋንጫ ርከክብ ለማድረግ በተዘጋጀ ሥነስርአት ላይ በጨረታ ለሽያጭ የቀረበ አንድ ቶርታ ኬክ አቶ ግደይ በርሄ በተባሉ ግለሰብ በ30 ሺህ ብር መገዛቱንና ግለሰቡም ለእለቱ ታዳሚዎች መጋበዛቸው ታውቃል።

በርክክቡ ላይ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ጨምሮ የሀገር መከላከያና የኦሮሚያ ፖሊስ ሠራዊት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

 

  ጅማ ግንቦት 22/2010(ኢዜአ)