ዜና ዜና

ፖል ካጋሜ ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ እና ጥረት ልምድ እንደምትወስድ ተናገሩ

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ እና ጥረት ሃገራቸው ልምድ እንደምትወስድ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ በትናንትናው እለት በሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ጉብኝት አድርገዋል።

በቆይታቸውም በፒ ቪ ኤች ጨርቃ ጨርቅ፣ ታል ቴክስታይል፣ ኦንቴክስ ኢትዮጵያ እና በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የጨርቃጨርቅ ማምረቻዎችን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላም በሀይሌ ሪዞርት ሆቴል ለፕሬዚዳንት ካጋሜ የዕራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በተዘጋጀላቸው የእራት ግብዣ ላይ ደስታቸውን ገልጸው፥ ከዶክተር አብይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽና የአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ተባብረው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ሩዋንዳን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሁለቱ ሀገራት ያለው የወንድማማች ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር በጋራ መስራት አለብን ያሉት ፕሬዚዳንት ካጋሜ፥ በክልሉ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተበረከተላቸው ስጦታም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሃገራቸውም ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ እና ጥረት ልምድ ትወስዳለችም ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ካጋሜ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው፥ ፕሬዚዳንት ካጋሜ ሩዋንዳን ከእርስ በእርስ ጦርነት ወደ ልማት የመሩ ፖለቲከኛ ናቸው ብለዋል።

በአህጉሪቱ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ካጋሜ ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ የአፍሪካ መስራች አባቶችን የሰላምና የልማት ራዕይ ለማሳካት በጋራ እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ካጋሜ ሃገር የመለወጥ አመራር ልምድ መውሰድ እንደሚቻል አንስተዋል።

አያይዘውም ፖል ካጋሜ በመሪነት ሚናቸው በሃገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለፕሬዚዳንት ካጋሜ ላም ከእነ ጥጃዋ በስጦታ ያበረከቱ ሲሆን፥ ፕሬዚዳንት ካጋሜም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የስዕል ስጦታ አበርክተውላቸዋል።

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)