ዜና ዜና

ማዕከላዊ ኮሚቴው የህዝቡን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ ስትራተጂያዊ ውሳኔዎች አስተላለፈ-ደኢህዴን

 የክልሉን መንግስት የሚመራው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሳዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ በህዝቡ ውስጥ የሚመላለሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችሉ ስትራተጂያዊ ውሳኔዎች ማስተላለፉን አስታወቀ፡፡

የማዕከላዊ ኮሚቴው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔዎችን ያሳለፈው ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በሀዋሳ ከተማ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነው፡፡

በስብሰባው ወቅታዊውን ክልላዊና ድርጅታዊ ሁኔታዎችን፣ የልማትና የመልካም አስተዳዳር የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

በዚህም የክልሉን ህብረ ብሔራዊነት የበለጠ በማጠናከር የተወዳዳሪነት አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ወሳኝና ስትራተጂያዊ ውሳኔዎች መተላላፋቸውን  ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔሮች ጋር በመሆን ያከናወኑት ተግባር በጋራ ለማደግና ለመልማት ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ  አቶ ተስፋዬ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

ወቅታዊ የሆነ  ክልላዊ ፣ የድርጅቱ ውስጣዊና ሀገራዊ ሁኔታዎችን በመገምገም  የልማት ፣የመልካም አስተዳደርና እስከ ክረምት የሚከናወኑ  ስራዎች ማዕከላዊ ኮሚቴው በሁለት ቀናት ቆይታው  የተወያየባቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሀገሪቱ እስከ መጋቢት ወር ድረስ የነበረው ሁኔታ ፈታኝ እንደነበርና የደኢህዴን ሊቀመንበር  የነበሩት የቀደሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ  ራሳቸውን የመፍትሄ አካል በማድረግ የወሰዱት አቋም ትክክለኛ መሆኑን በሰብሳበው መገምገሙም ተወስቷል፡፡

በስብሰባው የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማጠናከርና በየአካባቢው የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል እንቅፋትና ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን ለማስተካከል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በአቅጣጫውም መሰረት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ በከተሞች የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ ህዘቡን የሚያማርሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችንና አደረጃጀቶች ዙሪያ ጥናት እንዲካሄድ መወሰኑን የማዕከላዊ ኮሚቴው ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ አብራርተዋል፡፡

 ሀዋሳ ግንቦት 14/2010(ኢዜአ)