ዜና ዜና

የህግ ታራሚዎች ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የ3 መቶ ሺህ ብር ቦንድ ገዙ

የትም ሆኖ በሀገር ልማት ላይ ለመሳተፍ የሚገድብ ነገር የለም በማለት የህግ ታራሚዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ የ3 መቶ ሺህ ብር የቦንድ ግዢ ፈፀሙ፡፡

የግንቦት 20ን 27ኛ አመት የድል በአል ምክንያት በማድረግ የቦንድ ግዚ የፈፀሙት በአዲስ አበባ የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት፣ በሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ናቸው፡፡

የህግ ታራሚዎቹ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጋራና በተናጠል በመሆን የቦንድ ግዚ በመፈፀም ላይ እንደሚገኙ የማረሚያ ቤቱ ዋና ኦፊሰር አቶ አላምረው ተረፈ ተናግረዋል፡፡

በታራሚዎቹ ህብረት ሱቅ አማካኝነት ከዚህ ቀደም የ2መቶ ሺህ ብር የቦንድ ግዚ መፈፀሙንም አስታውሰዋል፡፡

ከታራሚዎች ህብረት ሱቅ ባሻገር ታራሚዎች በየግላቸው ከ33 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የቦንድ ግዚ ፈፅመዋል፡፡

ታራሚዎቹ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚደረጉ ሁለንተናዊ ለውጦችን በመገናኛ ብዙሀን እንደሚከታተሉና መንግስት ምህረት እንዲያደርግላቸውም ተስፋ አድርገዋል፡፡

ግንቦት 20፣2010/ኢቢሲ/