ዜና ዜና

በጊዜ የለንም መንፈስ፣ ብቃታችንን በማጎልበት ለአገር ግንባታ እንረባረብ!

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ
ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ.ም

በጊዜ የለንም መንፈስ፣ ብቃታችንን በማጎልበት ለአገር ግንባታ እንረባረብ!
መንግሥት፣ ህዝቡ በየደረጃው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ በማዳመጥ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል። ካስቀመጣቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎችም አንዱ አስፈጻሚ አካላት የሚሰጡትን አገልግሎት ፈጣን እና ውጤታማ ማድረግ፣ እንዲሁም የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራርን ማስፈን ነው።

ለዚህ ሲባል፣ አመራሩ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ፣ በጊዜ የለንም መንፈስ ብቃቱን እያሳደገ መሄድ እንደሚገባውና፣ ባጎለበተው አቅም ልክም የህዝቦችን ጥያቄዎች እየፈታ መሄድ እንዳለበት፣ ሥራ ተቆጥሮ እየተሰጠው፣ የሠራውን ቆጥሮ እያስረከበ መሄድ የሚጠይቀው ጊዜ ላይ እንደደረስን ይታወቃል።

የህዝቦችን የለውጥ ፍላጎትና መነቃቃት በሚመጥን መልኩ መንግሥት ምላሽ እየሰጠ መሄድ መጀመሩንም መገንዘብ ያሻል። ለአብነትም፣ በቅርቡ አስፈጻሚውን አካል መልሶ የማደራጀት ሥራ መከናወኑ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት በተለይም የኮንትሮባንዲስቶችን መረብ ለመበጣጠስ የተጀመረው ተግባር፣ የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሲባል በህግ ጥላ ሥር የነበሩ ዜጎችን ከእስር የመፍታት ሂደት መቀጠሉ፣ እንዲሁም በተለያዩ አገራት በወህኒ ቤት የሚገኙ ወገኖቻችንን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ከእስር እንዲለቀቁ የተጀመረው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ህዝቡ በተለያየ መልኩ የሚያነሳቸውን የፍትህ፤ የዕኩል ተጠቃሚነት፣ የህግ የበላይነት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መንግሥት በጥሞና በማዳመጥ ከራሱ ከህብረተሰቡ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመፍታት ቁርጠኝነቱን እያሳየ ይገኛል። በአንድ በኩል የማስፈጸም አቅሙን እያጠናከረ፣ በዚያው ልክ እና ፍጥነት የህዝቡን ጥያቄዎች የመመለስና ችግሮችን የመፍታት ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ፣ አሁን ጊዜው ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥበት ነው። ትውልዱ ለአገር ግንባታ እየተሯሯጠ ያለበት፣ የአገራችንን ሰላም፣ ልማት፣ ብልጽግናና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማጠናከር የሚረባረብበት ወቅት ነው።

በመሆኑም የፖለቲካ አመራሩም ይሁን የመንግሥት ሠራተኛው፣ በአጠቃላይ ዋነኛው ፈጻሚ የሆነው ህዝባችን ወቅቱ የሚጠይቀውን ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን ሁለንተናዊ ብቃት ተላብሶ የሚረባረብበት ወቅት አሁን ነው።