ዜና ዜና

በኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ ከአንድ ዓመት በላይ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ በስኬት ተጠናቀቀ

ለአንድ ዓመት ከሁለት ወራት ያህል በኢትዮጵያ ሱዳን እና ግብፅ የውጭ ጉዳይ፣ የውሃ ሀብት ሚኒስትሮች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ሲያደርጉት የነበረው እልህ አስጨራሽ ውይይት እና ድርድር አዲስ አባባ በተካሄደ ስብሰባ ትናንት ሌሊት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡

በታላቁ ህዳሴ ዙሪያ ድርድር ሲካሄድባቸው እና ስምምነት ላይ ሳይደርሱባቸው የቆዩ የተለያዩ ጉዳዮች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ከሱዳን እና ከግብፅ ስምምነት ተደርሶባቸዋል፡፡

ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር እስከ ሌሊቱ 9፡00 ሰዓት በተካሄደው የተሟሟቀ ክርክር ከመግባባት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

አንደኛ ከዚህ በፊት በግብፅ በኩል ልዮነቶችን በሌላ በሶስተኛ ወገን አደራዳሪነት እንዲፈታ የነበራት አቋም በማሰቀረቷ በግድብ አሞላልና የውሃ አለቃቅ (Filling and Operation) ላይ ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ጥናት ለማካሄድ ከሶስቱ አገሮች ከእያንዳንዳቸው አምስት አባላት የሚወከሉበት አንድ ቡድን ለሟቋቋም ተስማምተዋል፡፡

ሁለተኛ ቀደም ሲል በአማካሪው የቀረበው የጥናት ማስጀመሪያ ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያላቸውን የማብራሪያ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በተመለከተ ግብፅ ምንም አይነት አስተያየት ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለሁም የሚል አቋም ስታንፀባርቅ መቆየቷ የሚታወስ ነው፡፡ በትናትናው ስብሰባ በአማካሪው የቀረበው የጥናት ማስጀመሪያ ሪፖርት ላይ አገሮቹ ያላቸውን የማብራርያ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሶስትዮሽ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው ተደራጅተው ለአማካሪው በማቅረብ አማካሪው በሚሰጠው መልስ ላይ በቀጣይ ውይይት ለማድረግም ተወስኗል፡፡

ሶስተኛው የሃገራቱ መሪዎች በዓመት ሁለት ጊዜ በተራ በተራ በመዲናቸው ስብሰባ እንዲካሄድ ሚኒስትሮቹ ከመግባባት ደርሰዋል፡፡

አራተኛ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ፈንድን ለሟቋቋም እንዲችል የሶስቱ አገራት የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ግንቦት 26 እና 27/2010 ዓ.ም ካይሮ ተገናኝተው ፈንድ በሚቋቋምበት ሁኔታ ላይ ተወያይተው በሚኒስትሮቹ በኩል ለመሪዎች ቅርቦ ይፀድቋል ተብሏል፡፡

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ርወርቅነህ ገበየሁ ባደረጉት የመዝግያ ንግግር ከህዳሴ ግደብ ጋር በተያያዘ በእንጥልጥል ላይ በነበሩ ጉዳዮች ከመግባባት ተደርሷል፡፡
ሚኒስትሩ ስብሰባው በስኬት በመጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልፀው፣ በመግባባት ላይ የተደረሱ ጉዳዮች የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡

በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚያ ሹክሪ በበኩላቸው ውይይቱ የተካሄደበት መንፈስ ግልፅነት እና ወንድማማችነት የተሞላበት እንዲሆን በመግልፅ መግባባት ላይ እንዲደረስ ኢትዮጵያ ላደረገቸው አስተዋፅኦ አመስግነዋል፡፡

የሱዳን ውሃ ሚኒስትር ሙታዝ ሙሳ ይህ ውጤት ከአንድ ዓመት በላይ እልህ አስጨረሽ ጥረት በኋላ መገኘቱን ትልቅ ትምህርት ያለምንም የሶስተኛ የውጭ ጣልቃ ገብነት በጋራ ጉዳዮችንን መፍታት የቻልንበት ነው ብለዋል፡፡መረጃው የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ነው።

ግንቦት8/2010