ዜና ዜና

የፌዴራል መንግስት የካቢኔ አባላት በኃላፊነት የሚቆዩት በሚኖራቸው የሥራ አፈፃፀም ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

የፌዴራል መንግስት የካቢኔ አባላት የሥራ ኃላፊነት የቆይታ ጊዜ የሚወሰነው ኃላፊዎቹ በሚኖራቸው የሥራ አፈፃፀም ምዘና መሰረት ብቻ አንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያስታወቁት ዛሬ ለካቢኔ አባላትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ወደ ፊት ሊከናወኑ በታቀዱ የመንግሰት ተግባራትና የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ገለፃና መመሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ገለፃቸው እያንዳንዱን የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች ከመጪው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር የሥራ ውል ስምምነት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በዚህም ሚኒስትሮቹ ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ሥራ ቆጥረው በማስረከብ አፈፃፀማቸው እየተለካ ባላቸው ውጤት መሰረት ኃላፊነት ላይ እንደሚቆዩ ገልፀዋል።

በዓመቱ መጨረሻ በቋሚ ኮሚቴ የሚገመገሙ ሚኒስትሮች በቀጥታ ለህዝብ ክፍት በሆነ ጥያቄ ይገመገማሉ፤ በግምገማው መሰረት ኃላፊነታቸውን በውጤታማነት ያልፈፀሙ ሥልጣን ላይ እንደማይቆዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

አሰራሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ለህዝብ የገባውን ቃል የሚፈጽም ተቋም መሆኑ የሚታይበት ይሆናል ብለዋል።

የገባውን ቃል አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ያልፈፀመ ኃላፊ ደግሞ በማግስቱ የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድበት እንደሚሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

"ይህ የተጠያቂነት ስርዓት ለህዝብ ክፍት በሚሆንበት ጊዜ ኃላፊዎችም ጠንክረው እንዲሰሩ፣ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር የሚያደረግ ነው፤ ይህም በመንግስት አስተዳደሩ ውስጥ ተጠያቂነት መኖሩን ያረጋግጣል" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ዶክተር አብይ አክለውም የካቢኔ አባላቱ በሚመሯቸው መስሪያ ቤቶች ከሰራተኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ቀለል ያለ እና ውጤታማነትን ማዕከል ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የካቢኔ አባላት በሚመሯቸው ተቋማት የመጀመሪያ ተግባራቸው ሊሆን የሚገባው "በመስሪያ ቤቶቹ ያለውን ንጽህና ጨምሮ ሌሎች ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሥራን አልመው የሚዘጋጁ ስብሰባዎችም አጭርና ውጤታማ በሆነ መንገድ መከናወን አንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። 

ከዚህ ቀደም በየሳምንቱ እለተ ዓርብ ይካሄድ የነበረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ካቢኔ ስብሰባ ወደ ቅዳሜ እንዲዛወር መወሰኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ አስታውቀዋል።

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010/ኢዜአ/