ዜና ዜና

በአራቱም ታዳጊ ክልሎች ሰፋፊ የግብርና መካናይዜሽን ልማት ሊካሄድ ነው

በአራቱም ታዳጊ ክልሎች የሚገኘው ሰፋፊና ለም መሬት በመካናይዜሽን በማልማት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በሚኒስቴሩ የግብርናና እንስሳት ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ወንዳለ ሀብታሙ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሊታረስ የሚችል 74 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖራትም እየታረሰ ያለው ግን 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ ነው ።

በሶማሌ ፣ በአፋር ፣ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ገና ያልተነኩ ሰፋፊና ለም መሬት እንዳለ አመልክተው ይህንኑ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ እንደማይቻል መንግስት ግንዛቤ መያዙን ተናግረዋል ።

በአራቱ ታዳጊ ክልሎች ከሌሎች አንፃር በቂ የሰው ጉልበት የማይገኝ በመሆኑ፣ ከመሬቱ ስፋትና ከምርታማነት ማሳደግ ጋር ተያይዞ የመካናይዜሽን ግብርና ለማስፋፋት መታቀዱን ዳይሬክተር ጄነራሉ አስረድተዋል ።

" ሀገራችን አሁን ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው በግብርናው ላይ መዋቅራዊ ሽግግር ሲመጣ ብቻ ነው" ያሉት አቶ ወንዳለ ያለንን ሀብት አሟጥጠን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ ሰፋፊ እርሻ ልማቶች ለማካሔድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የሀገሪቱ የግብርና ምርቶች ተፈጥሮዊ ይዘታቸው የጠበቁ በመሆናቸው በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ፣ በአውሮፓና በኢሲያ ገበያዎች ያላቸውን ተፈላጊነት ከፍተኛ ነው፡፡

የግብርና ምርቶችን በብዛትና በጥራት አምርቶ ለማቅረብ የግብርና መካናይዜሽን የሚያስፈልግበት ምዕራፍ ላይ መደረሱን ያመለከቱት ዳይሬክተር ጀነራሉ የመካናይዜሽን በሌሎች ክልሎች ጭምር የሚገኙ ቆላማ አካባቢዎችም እንዲለማ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ በበኩላቸው የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት የምግብና የስነ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅማችን ለማጎልበትና ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት ወሳኝነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በአፋር ክልል በሙከራ ደረጃ 700 ሄክታር መሬት በመካናይዜሽን እንዲለማ ተደርጎ በአማካይ 35 ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ የስንዴ ምርት በሄክታር መገኘቱ በቆላማ አካባቢዎች የመከናይዜሽን ግብርና ለማካሔድ የተያዘውን እቅድ የሚያነቃቃ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሶማሌ ክልል ጎዴ አካባቢ በሩዝና በሙዝ ላይ የተደረገው ሙከራ ውጤታማ እንደሆነ መረጋገጡን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው በሄክታር በአማካይ ከ45 ኩንታል በላይ ጥራቱንና ይዘቱን የጠበቀ የሩዝ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ አመላክተዋል።

የግብርናው መካናይዜሽን ልማት በመስኖ የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው "በቦይ ውሃ ማጠጣት የአፈርን ጨዋማነት የሚጨምር በመሆኑ ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል" ብለዋል ።

በተቀናጀ የግብርና ፓኬጅና በመካናይዜሽን ላይ ከ300 በላይ የአፋርና የቤንሻንጉል ጉሙዝ የግብርና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የአምስት ቀናት የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል ።

ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ፣ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምርና ከሌሎችም የተወጣጡ ምሁራን በአሰልጣኝነት እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

ግንቦት6/2010/ኢዜአ/