ዜና ዜና

በምዕራብ ሐረርጌ የግብርና ግብአት ፍላጎት ማደግ ምርታማ እያደረገ ነው

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አርሶአደሮች በግብርና ግብአቶች ፍላጎትና አጠቃቀም ላይ የነበራቸው ግንዛቤ በማደጉ ምርትና ምርታማነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ተናገሩ ።

አርሶ አደሮቹ በመጪው የመኸር አዝመራ አስፈላጊውን የግብርና ግብአቶች በመጠቀም ለተሻለ ምርታማነት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

በሀብሮ ወረዳ ዋጩ ቀበሌ አርሶ አደር ይልማ በቀለ ባለፉት ሦስት ዓመታት በቂና የተመጣጠነ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅመው በመዝራታቸው የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ምርጥ ዘርና ማዳበርያ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ የሚያመርቱት ምርት ከበፊቱ በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በሁለት ጥማድ መሬታቸው ላይ ማዳበሪያ ሳይጠቀሙ ከ5 እስከ 6 ኩንታል ማሽላ ያገኙ የነበረው በአሁኑ ወቅት ከ9 እስከ 10 ኩንታል ከፍ ማለቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

"ቀደም ባሉት ዓመታት ማዳበሪያ መጠቀም መሬት ያበላሻል የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበረኝ" ያሉት አርሶአደሩ፣ በዚህም እራሳቸውን ጎድተው መቆየታቸውንና በአሁኑ ወቅት በግብርና ባለሙያዎች ጥረት እውነታውን መረዳታቸውን ገልጸዋል።

የማዳበሪያን ጥቅም በአግባቡ በመረዳታቸው በመጪው የመኸር አዝመራ የሚጠቀሙበት አራት ኩንታል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመግዛት በመስመር ለመዝራት ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የአካባቢው አርሶ አደር ለይኩን ጋሻው የተመጣጠነ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀም በሄክታር ያገኙት የነበረውን የማሽላ ምርት ከ15 ኩንታል ወደ 35 ኩንታል ማሳደግ እንደቻሉ አስረድተዋል።

ማዳበሪያ በብድር ወስደው ከሚያለሙት አምስት ጥማድ መሬት ምርታቸው መጨመሩን የገለጹት በገመቺስ ወረዳ የሰባሌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ለገሰ ይፈሩ በአሁኑ ወቅት ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቀድመው ገዝተው የሚጠቀሙበት አቅም መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽፈት ቤት የእርሻ ምርትና የግብአት አቅርቦት ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ወይዘሮ ምሳዬ ደሳለኝ እንደገለፁት በዞኑ የአርሶ አደሩ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ፍላጎት እያደገ መጥቷል።

የአርሶአደሩን ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም ለመኸር እርሻው እስካሁን ድረስ 38 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 2 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር መሰራጨቱን ገልጸው፣ ለአዝመራው የሚያስፈልግ ተጨማሪ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ ለማቅረብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል

ጽህፈት ቤቱ ከአርሶ አደሩ ያሰባሰበው የፍላጎት መረጃ
እንደሚያመላክተው ከሆነ በዞኑ ለዘንድሮው የመኸር አዝመራ ከ75 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ከ7 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡

ግንቦት1/2010 /ኢዜአ/