ዜና ዜና

'ፋኦ' ሚስተር ዴቪድ ፈሪን በአዲስ አበባ የክፍለ አህጉሩ አስተባበሪ አድርጎ ሾመ

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ሚስተር ዴቪድ ፊሪን በአዲስ አበባ የምስራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉራዊ አስተባበሪ አድርጎ ሾመ።

ፋኦ ከህዳር 10 እስከ 17 ቀን 1998 ዓ.ም በጣልያን ርዕሰ መዲና ሮም ባካሄደው 33ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ማስተባበሪያ ቢሮ መቀመጫ እንድትሆን መወሰኑ የሚታወስ ነው።

ቢሮውም መጋቢት ወር 2000 ዓ.ም ተከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

ሚስተር ዴቪድ ፊሪን ፋኦ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ የሚያስተባብሩ አዲስ ተሿሚ አድርጎ መሾሙን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ አዲሱን የፋኦ ተሿሚ ዴቪድ ፊሪን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ መልካም ግንኙነት እንዳላት በመጥቀስ ድርጅቱ አገራችን ከድህነት ለመላቀቅ የምታደርጋቸውን ጥረቶች በተለይም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን በማሳካት ዙሪያ ለኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኑን ገልጸዋል።

ፋኦ በአጠቃላይ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው፤ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች እውን ለማድረግና ከድርቅ ለመላቀቅ ከድርጅቱ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ተናግረዋል።

አዲሱ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ፋኦ የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ አስተባባሪ ሚስተር ዴቪድ ፊሪን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምርታማ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ድርጅቱ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸውን መግለጫው አትቷል።

የጣልያን ርዕሰ መዲና ሮምን ዋና መቀመጫ ያደረገው የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ፋኦ የተቋቋመው በ1938ዓ.ም ነው።

ድርጅቱ በ1974 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተወካይ ከላከ ጊዜ ጀምሮ ዋነኛ የኢትዮጵያ የልማት አጋር እንደሆነ ይጠቀሳል።

ፋኦ ባለፉት አሰርት ዓመታት በኢትዮጵያ በግብርናና አካባቢ ጥበቃ ወጪያቸው ከ55 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ ከ100 በላይ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ግንቦት 1/9/2010/ኢዜአ/