ዜና ዜና

የህዳሴ ሰላም ዋንጫ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ምዕራብ ዕዝ ደረሰ

የህዳሴ ሰላም ዋንጫ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ማዕከላዊ ዕዝ የነበረው ቆይታ በማጠናቀቅ ምዕራብ ዕዝ ደረሰ፡፡

የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጀነራል ዮሐንስ ወልደ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ለምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጀነራል ፍሰሀ ኪዳኑ በሁመራ ከተማ አስረክበዋል፡፡

በዋንጫው ርክክቡ ስነ ስርዓት ወቅት የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ እንደገለጹት ሰራዊቱ ድንበር ከማስከበር ባሻገር ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዥ በመፈጸም ድጋፍ አድርጓል፡፡

የዕዙ አባላት እስከ አሁን ከ78 ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያለው ቦንድ በመግዛት መደገፋቸውንም አመልክተዋል፡፡

የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ በበኩላቸው "ዋንጫው በዕዙ ለአንድ ወር ቆይታ ያደርጋል"ብለዋል፡፡

በቆይታው የሰራዊቱ አባላት ቦንድ በመግዛት የህዳሴ ግድብ ያላቸውን አጋርነት ለማረጋገጥነ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የዕዙ አባላት ከአሁን በፊት ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ቦንድ መግዛታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የሰላም ህዳሴ ዋንጫ ወደ ዕዙ መግባቱን ተከትሎ ቦንድ ግዥው እንደሚቀጥልም አመልክተዋል፡፡

በዋንጫው ርክክብ ስነ ስርዓት ወቅት ከተገኙት መካከል የ24ኛ ክፍለጦር አባል ወታደር ዳኝነት ተስፋ በሰጠው አስተያየት በዓመት የሚከፈል የአንድ ወር ደመወዙን ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ እንዲውል ቦንድ ለመግዛት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ከአሁን በፊት ከ11ሺህ ብር በላይ ቦንድ ከመግዛቱም በተጨማሪ አሁንም ለመፈጸም ዝግጁ መሆኗን የገለጸችው ደግሞ ሌላው የሰራዊቱ አባል የአስር አለቃ ወርቃየሁ መኮንን ናት፡፡

ሚያዝያ 27/2010 /ኢዜአ