ዜና ዜና

ውስጣዊ ጥንካሬያችን ለውጫዊ ገጽታችን መቀየር ጽኑ መሰረት ነው !

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ-ሚያዝያ 26 ቀን 2010 ዓ.ም

ውስጣዊ ጥንካሬያችን ለውጫዊ ገጽታችን መቀየር ጽኑ መሰረት ነው !

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰሞኑን ጂቡቲን እና ሱዳንን ጎብኝተው ተመልሰዋል። የሥራ ጉብኝታቸው ከሁለቱ ጎረቤት አገራት ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና ትስስርን ለማጠናከር ያለመ ነበር።

እንደሚታወቀው፣ የቅርብ ጎረቤቶቻችን ከአገራችን ጋር የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ ሃብት ወዘተ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ በአገራችን የሚካሄደው ለውጥ እነሱን በቀጥታ የሚነካ ሲሆን፣ በእነሱ ውስጥ የሚካሄደው ለውጥም የዚያኑ ያህል እኛን በቀጥታ የሚነካ ነው።

ይህንኑ ዕውነታ ታሳቢ በማድረግ አገራችን ኢትዮጵያ ከአካባቢ አገራት ጋር በመልካም ጉርብትና፣ በትብብርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ስታራምድ ቆይታለች፤ አሁንም እያራመደች ትገኛለች፡፡ በዚህም ከኤርትራ በስተቀር ከሌሎች አጎራባች አገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እና ትስስር መፍጠር ችላለች። ከኤርትራም ጋር ቢሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማካሄድ ጀምራለች።

አገራችን ኢትዮጵያ የአካባቢዋን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ስትል ረጅም ርቀት ተጉዛለች፤ ሌሎች አገሮችን በማስተባበርም የላቀ ሚና ተጫውታለች። ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚበጁ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እና የልማት እቅዶችን አውጥታ በመንቀሳቀስ፣ ጎረቤቶቿ በተቸገሩ ሰዓት በማስጠለል እና ያላትን ቆርሳ በማካፈል ለመልካም ጉርብትና እና የጥቅም ትስስር ጉልህ ሚና እየተጫወተች ያለች አገር ናት።

በውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን ላይ እንደተመለከተው የቅርብ ጎረቤቶቻችንም ይሁኑ ሌሎች አገራትን አስመልክቶ የምንከተላቸው የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች የሚያጠነጥኑት ሰላማችንን፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማታችንን እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችንን በማረጋገጥ እና በማገዝ ላይ ነው፡፡ ይህም ሕዝቦቻችን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ዕውን ከማድረግ አኳያ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር እና በአገራችን ህልውና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎችን ማስወገድን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ከቅርብ ጎረቤቶቻችን ጋር የምንፈጥረው መልካም ግንኙነት እና ትብብር በውስጥ ጥንካሬያችን ላይ ተመስርቶ፣ ተመልሶ ለእኛው ትልቅ አቅም የሚፈጥርልን መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

ሰሞኑን እንደተስተዋለው፣ በአገራችን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ ቀጥሏል፡፡ በግዙፍነታቸው የሚታወቁ የውጭ ኩባንያዎች ወደ አገራችን እየገቡ ይገኛሉ፡፡ ትላልቅ የንግድ ኤግዚቢሽኖች በውጭ እና በአገር ውስጥ መካሄዳቸው የቀጠለ ሲሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ አበዳሪ ተቋም እንዳረጋገጠውም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዕድገቷ በአፍሪካ የመሪነቷን ቦታ ከጋና ትረክባለች፡፡

በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአሜሪካ፣ የጀርመንና የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአገራችን ተገኝተው ያካሄዷቸው የሥራ ጉብኝቶች የሚያረጋግጡልንም፣ በአስቸጋሪ ወቅት ላይ በነበርንበት ጊዜ እንኳ አገራችን በሰላም፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በሌሎችም ዘርፎች ተፈላጊነቷ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ነው፡፡

ለተፈላጊነታችን መጨመርም ዋነኛው ምክንያት በውስጣችን የፈጠርነው ጠንካራ አቅም መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመደማመጥ እየፈታን እስከሄድን ድረስ በመላው ዓለም የሚኖረን ተሰሚነትና ተቀባይነት እየጨመረ መሄዱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በመሆኑም፣ ውስጣዊ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ እየፈታን፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን እያጠናከርን፣ ልማታችንን ለማስቀጠል በአገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሥራ ከዳር ለማድረስ እና የአገራችንን በጎ ገጽታ ለመገንባት መላው ሕዝባችን ከመንግስት ጎን ተሰልፎ እንዲረባረብ ጥሪውን ያቀርባል፡፡