ዜና ዜና

በህጋዊነት ሽፋን በአዲስ መልክ የተጀመረውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በጋራ እንከላከል!

ሚያዝያ 25/2010 ዓ.ም

በህጋዊነት ሽፋን በአዲስ መልክ የተጀመረውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አስመልክቶ በፌዴራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተዘጋጀ ፕሬስ ሪሊዝ

በህጋዊነት ሽፋን በአዲስ መልክ የተጀመረውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በጋራ እንከላከል!

የኢፌዴሪ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ዜጎች በውጭ አገር መስራት እስከፈለጉ ድረስ በህጋዊ መንገድ የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አዋጅ በ2008 ዓ.ም ማፅደቁ ይታወቃል። ይህንኑ ተከትሎ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከጥቅምት 2006 ዓ.ም ጀምሮ ተጥሎ የነበረውን የውጭ አገር ስራ ስምሪት ዕግድ ማንሳቱ ይታወሳል፡፡ ዜጎች በውጭ አገር መስራት የሚችሉት በአዋጁ የተመለከቱትን ቅድመ ሁኔታዎች ሲያሟሉ ብቻ መሆኑንም በወቅቱ ማስገንዘቡ ይታወሳል።

በአዋጁ መሰረት ዜጎች በህጋዊ መንገድ በውጭ አገር ለመስራት ዕድሜያቸው ቢያንስ 18 ዓመት የሆነ፣ የትምህርት ደረጃቸው ቢያንስ ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ሊሆን እንደሚገባና በሚሄዱበት አገር ለስራ የሚያግዛቸው በቂ ክህሎት ይኖራቸው ዘንድ በየአካባቢያቸው ካሉ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት አስፈላጊውን ሥልጠና መውሰድና የብቃት ምስክር ወረቀት መያዝ እንደሚገባ ተደንግጓል።

በተጨማሪም ህጋዊ እውቅና ባለው ኤጀንሲ ተመልምለው መቅረብ እንዳለባቸውና በሚሄዱበት አገር ጥቅማቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው የሚጠበቅላቸው ስለመሆኑ አስፈላጊው የስራ ውል በውጭ አገር ካሉ ተቀባዮቻቸው መፈረሙ ከተረጋገጠ በኋላ ሁሉም ነገር መሟላቱን የሚገልፅ መታወቂያ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሰጣቸው ብቻ መሆን እንዳለበት በአዋጁ በግልጽ ተቀምጧል፤ መግለጫም ተስጥቶበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአዋጁ አፈፃፀም ሲባል የኢፌዴሪ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ከአንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጋር የህጋዊ ስራ ስምሪት ስምምነቶች መፈራረሙን የሚገልፅ መረጃ በሚዲያዎች ሲቀርብ ቆይቷል። በመሆኑም አንዳንድ ህገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ኢትዮጵያ የተፈራረመቻቸው ስምምነቶች ተግባራዊ መደረግ እንደጀመሩ አስመስለው ዜጎቻችንን በማጭበርበር በውጭ አገር ካሉ አዘዋዋሪዎች ጋር በተቀናጀ መልኩ በቱሪስት ወይም በአገር ጎብኚ ስም ወደተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እየላኩ መሆናቸው ተደርሶበታል።

አገራችን ኢትዮዽያ የዜጎችን በውጭ አገር የመስራት መብት ከማክበርና ከማስከበር አኳያ ከኳታርና ጆርዳን መንግስታት ጋር የተፈራረመቻቸው ህጋዊ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ስምምነቶች ጸድቀዋል። ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር የተፈረመው ስምምነት ደግሞ በህገመንግስታችን አንቀጽ 9 (4) ላይ በተደነገገው መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርብ ጊዜ ጸድቆ ስራ ላይ የሚውል ይሆናል፡፡ ከኩዌት፣ ሊባኖስ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር መንግሥት ገና በድርድር ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ስምምነቶቹ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቁ በኋላም ቢሆን ተጓዦች በውጭ አገር መስራት የሚችሉት ከላይ የተገለፁትንና ሌሎች በአዋጁ ላይ የተዘረዘሩትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑንም መገንዘብ ያሻል። እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ ያስፈለገው ዜጎቻችን ለስራ በሚሄዱባቸው አገራት መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው መጠበቁን ለማረጋገጥ ሲባል መሆኑን መረዳትም ይገባል።

ይሁንና ህገወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች በየጊዜው ለህዝብ ይፋ የተደረጉ አንዳንድ መረጃዎችን በሚያመቻቸው መንገድ እየቆራረጡና እየቀጣጠሉ ዜጎቻችንን በማወናበድ ከአገሮቹ ጋር የተደረጉት ስምምነቶች ህጉ በሚያዘው መሰረት ባልፀደቁበትና ሥራ ላይ ባልዋሉበት እንዲሁም በአዋጁ ላይ በግልፅ የሰፈሩት ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ዜጎቻችንን ወደተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እየላኩ መሆናቸው ተደርሶበታል። 
አብዛኞቹ በአገር ጎብኚ ስም ወደተጠቀሱት አገራት እየተላኩ ያሉት ገና በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ፣ ቪዛ በስማቸው እስከመጣላቸውና አውሮፕላን እስከተሳፈሩ ድረስ ጉዟቸው ህጋዊ የሚመስላቸው ጥሩና መጥፎውን እምብዛም የማይለዩ የገጠር ወጣት ሴቶች መሆናቸው ታውቋል። እነዚህ ወገኖች በዚህ መልኩ ወደ ባዕድ አገር ከሄዱ በኋላ በቤት ሰራተኛነት ስለመስራታቸው ምንም ዋስትና የሌለና ቢሰሩም መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆላቸው እንደማይሆን መገመት አያዳግትም።

በአጠቃላይ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ለስራ የሚደረገው ጉዞ በውጭ አገር ስራ ስምሪት አዋጅ፤ ደንብና መመሪያ ላይ የተጠቀሱት መስፈርቶችና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሟሉ ድረስ በህጋዊነት ስም ወደ ተጠቀሱትም ይሁን ወደ ሌሎች አገራት ለስራ ሲባል የሚደረግ ጉዞ ህገ ወጥ መሆኑን መላው ህብረተሰብ መገንዘብ ይገባዋል። ስምምነቶቹ ከፀደቁ በኋላም በአዋጁ ላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች ማሟላትና ለዚህም ሲባል አስፈላጊውን የብቃት ማረጋገጫ ሰነድና የስምምነት ውል ሳይዙ መሄድ በተግባር በረሃዎችንና ውቅያኖሶችን አቋርጦ ከመሄድ ያልተለየና የዜጎቻችንን ህይወት ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ህገወጥ ስደት መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

በመሆኑም ይህን በመሰለው ህገወጥ ተግባር ላይ በተሰማሩ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ላይ መንግሥት የሚያደርገው ቁጥጥርና የሚወስደው እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ በዋነኝነት የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑት ወጣቶችና ወላጆች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መንግሥት ያሳስባል። 
መገናኛ ብዙሃንም የችግሩን አስከፊነት በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ከመሆኑ አንፃር ህብረተሰቡ በህጋዊነት ስም እየተካሄደ ካለው ህገወጥ ተግባር ራሱን እንዲጠብቅ በተከታታይ በማሳወቅና በማስተማር አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

ዜጎች ለስራ ያላቸውን አመለካከት እስከቀየሩ ድረስ ባህር ማዶ ሄደው ከሚሰሩት በተሻለ በአገራቸው ሰርተው መለወጥ የሚችሉበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል። ይህም ሆኖ በውጭ አገር የመስራት ፍላጎት ካላቸው መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ መሆኑን ማረጋገጥ የሚገባቸው ሲሆን ከዚህ አንፃር ህጋዊ የሥራ ስምሪቱን አሰራር በመከተል ብቻ እንዲጓዙ መንግሥት ይመክራል።

ስደት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በየትኛውም አገር ያለና የሚኖር ነው። አገራችንም ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካውያን ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች። ዋናው ነገር ዋስትና በሌለው ህገወጥ ስደት ወደ ውጭ መጓዝ ራስን ለአደጋ የሚያጋልጥ፣ ጉዳቱም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብና ለአገርም ጭምር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። 
ስለዚህ ህጋዊ የስራ ስምሪትን ተከትሎ የሚጓዝ ማንኛውም ዜጋ የውጭ አገር ስራ ስምሪትን ለማስፈጸም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 923/2008 የሚጠይቀውን መስፈርት በማሟላት በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ውላቸው ጸድቆና ለተጓዡም ልዩ መታወቂያ ተሰጥቶት እስካልሄደ ድረስ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ጉዞ ሁሉ ህገወጥ መሆኑን ሁሉም ህብረተሰብ ና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገንዝበው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መንግሥት በአጽንኦት ያሳስባል።