ዜና ዜና

”ህግና ዴሞክራሲ ፍትህና ቅልጥፍናን የሚያረጋግጡ መሳሪያዎች እንጂ ስራን የሚያጓትቱ መሆን የለባቸውም”-ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ

የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፤ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩበት፤ከፖለቲካ ወገንተኝነት ከጉቦ የጸዳ አገልግሎት የሚሰጥበት እንዲሆን "ህግና ዴሞክራሲ ፍትህና ቅልጥፍናን የሚያረጋግጡ መሳሪያዎች እንዲሆኑ መንግስት በትኩረት የሚሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት "የፍቅር እና የአንድነት ኪዳን" በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ህዝባዊ መድረክ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ 25 ሺህ ለሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ነው ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት በህግና መመሪያ ተከልሎ የሚደረግ አድሎና በደል በማቆም በፍትህ ስርዓቱ ህዝቡ እውነተኛ ዳኝነት የሚያገኝበት ፤የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፤ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩበት፤ከፖለቲካ ወገንተኝነት ከጉቦ የጸዳ አገልግሎት የሚሰጥበት እንዲሆን አበክረን እንሰራለን ፡፡

ዴሞክራሲን መገንባት የጋራ ስራን የሚጠይቅ ከባድ ስራ መሆኑን በማውሳት ለሁላችንም ነጻነት የሚያጎናጽፈንን ያክል የሃይለኛውን የባለጸጋውን ፤የባለጉልበቱን የባለጸጋውን፤የማድረግ አቅም የሚወስንና ለሰዎች ልቅ ፍላጎት ልጓም የሚያበጅ ፤ዜጎችን ሁሉን በህግ ፊት እኩል የሚያደርግ በራሱ ሂደትም ግብም የሆነ በቀላሉ የማይደፍን ስርዓት መሆኑንን መዘንጋት አይገባም ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም ትርጉም ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብት ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም መጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ከዚህ አንጻር ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ታማኒነት ያለው፣ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ ላይ ሚከናወን እውነተኛ ፉክክርና የሃሳብ ፍጭት የሚታይበት እንዲሆን ለማድረግ ከወዲሁ በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

የዴሞክራሲ እውነተኛ ጥንካሬ መለኪያና አመላካች ተደረገው ትልቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው መካከል የፍትህ ስርዓት ስርዓቱ ተቋማዊና ሙያዊ ብቃት በቀዳሚነት እንደሚይዙ የጠቆሙት ዶክተር አብይ የህዝባችን ብሶት ምንጭ የሆኑት የፍትህ አካላት ነጻነታቸውንና ሙያዊ ስነ-ምግባራዊ ብቃታቸውን ባረጋገጠ መልኩ እንዲሰሩ በህገ መንግስቱ መሰረት ተጠያቂ እንዲሆኑና የፍትህ ስርዓቱ ላይ ለውጥ እንዲመጣ የሚያስችሉ መፍትሄዎችን በመውሰድ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ለህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲ ስርዓት መረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠናክረው ከወገንተኝነት ጸድተው ህዝባዊነታቸው እንዲጎለብት መወሰድ ያለባቸው ቁልፍ እርምጃዎች ጥናትን መሰረት ያደረጉ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አንስተዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም እንዳብረሩት አገራችን ላይ እንዲሆን የምንፈልገውን መልካም ነገር ሁሉ ወደ መሬት ለማውረድና በተጨባች ምኞታችን እውን ለማድረግ የአገራችን መገናኛ ብዙሃን ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ዘርፉ ባሁኑ ወቅት ብልጽግናና ዴሞክራሲን ከማስፈን አኳያ ያለው ሚና በቂ ተደርጎ አይወሰድም ብለዋል ፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ፣የብሮድካስትና የህትመት ሚዲያዎች ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገት እስካሁን ከሰሩት ይልቅ ወደፊት የሚሰሩት እንደሚበዛ መንግስት ይተማመናል ነው ያሉት፡፡

ሁሉንም የሚዲያ ተቋማት፣ጋዜጠኞች፣ሌሎች የሚዲያ ባለሞያዎች፣አመራሮች፣ባለቤቶች ገና በማደግ ላይ ያለውን ይህንን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የተጋተሩ አካላት በሙሉ በአገር ግንባታና በትውልድ ቀረጻ እንዲሁም ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ዘርፍ መሆኑን ተገንዝበው በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሚያዝያ 7/2010/የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት/