ዜና ዜና

በኢኮኖሚያችን ላይ ታይቶ የነበረው አንጻራዊ መቀዛቀዝ ለማነቃቃት በትኩረት ይሰራል- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ

በአገራችን ተፈጥሮ የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት ባጠቃላይ ኢኮኖሚያችን ላይ ጥሎት ያለፈውን ጠባሳ ሰላምን ይበልጥ በማረጋገጥ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እንደሚሰራ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናግረዋል።

ክቡር ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት "የፍቅር እና የአንድነት ኪዳን" በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ህዝባዊ መድረክ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ 25 ሺህ ለሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ነው ፡፡

"የሀገራችን ኢኮኖሚ እንደ ነዳጅ ባሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ሳይሆን በዜጎቻችን ላብ እና የማያባራ ጥረት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የሕዝባችን የዕለት-ተለት እንቅስቃሴ አንድ ቦታ ላይ እክል ሲገጥመው ሙሉ ኢኮኖሚያችን ችግር ይገጥመዋል፡፡ የኢኮኖሚያችን ሁለንተናዊ ትርታ የሚነሳውና ማደግ መመንደጉም እርግጥ የሆነ ህልውናውን እንደተጎናጸፈ የሚጓዘው፣ የህዝባችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመደበኛ ፍሰቱ መቀጠል ሲችል ብቻ ነው፡፡" እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚንሰትሩ ገለጻ፡፡

በመሆኑም ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በአገራችን ተፈጥሮ የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት ባጠቃላይ ኢኮኖሚያችን ላይ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይሁን እንጂ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን እጅለእጅ ተያይዘን በፍጹም ቁርጠኝነት በጋራ አስከሰራን ድረስ ያንን ማካካስ የሚያስችል በቂ እድል በራሳችን መዳፍ ውስጥ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

አርሶ አደርና አርብቶ አደሩ ፤የመንግስት ሰራተኛውና ነጋዴው፤ተማሪና መምህሩ፤ወጣት አዛውንቱ፤ወዘተ በሰላም እጦት የኢኮኖሚ ግስጋሴያችን እንዳይገታ በሃላፊነት ስሜት ሁሉም የአገሩን ሰላም በመጠበቅ ዘብ እንዲቆምም ጠይቀዋል፡፡

የማምረቻ ዘርፉን ማጠናከርና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን አቅም በማጠናከር ምርቶችን በማብዛት ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ለውጭ ምንዛሪ ብክነት ምክንያት እየሆኑ ባሉ ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ ክትትል በማድረግ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም አስረድተዋል።

መንግስት አሁን ላይ በህዝቡ ዘንድ የታየውን ተስፋ እውን ለማድረግ በጽናት እንደሚሰራ ጠቁመው ህዝቡም ባለፉት አመታት በአንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመካስ መስራት ይገባዋል ብለዋል።

"ወደኋላ መመለስ ወይም ጥቂት ወደ ኋላ መራመድ ማለት ሁልጊዜ ወደኋላ መመለስ ላይሆን ይችላል ፤ምልሰቱ እንደመለሰን ሲያስቀር ሽንፈት ቢሆንም ወደፊት ሲያንደረድር ግን የድል መሰረት ነው"፡፡ በዚህም አንጻር በኢኮኖሚያችን ላይ ታይቶ የነበረው አንጻራዊ መቀዛቀዝ ለመንደርደር እንደመመለስ የብልህ ተግባር ቆጥረን ወደ ፊት ተንደርድረን ካሰብንበት የመድረሻ መልካም አጋጣሚ የምናደርግበት እድል በእጃችን ነው መሆኑን ነው ክቡር ጠቅላይ ሚንሰትሩ ያስረዱት፡፡

ባሁኑ ወቅት በመሰረተ ልማት ግንባታ በስፋት እንደመሰማራታችን መጠን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማጋጠሙ የሚጠበቅ ቢሆንም ችግሩ ከቁጥጥር እንዳይወጣና ከስር መሰረቱ እንዲቀረፍ አስተማማኝ የሆነ የገቢና ወጭ ንግድ ስርዓት እንዲሰፍን የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ወደ ውጭ በመላክ በትጋት የሚሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የንግድ ስርዓታችን ከአስመጭነት ይልቅ የአገር ውስጥ አምራቾችን በሚያበረታታ ሁኔታ እንዲቃኝ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ባላሀብቶች መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ብቻ ሳይሆን እንዳያሸሹ ምቹ የሆነ የአስተዳደር አቅም በመፍጠር በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ሃገር በቀል ድርጅቶች እንዲበዙ ልዩ ድጋፍና ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሬ ብክነት በመቀነስ ለዚህ ችግር ተጋላጭ የሚሆኑ ዘርፎች ላይ በተለይም ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ ቀጥተኛ ክትትልና ምርምር በማካሄድ በፍጥነት የሚጠናቀቁ መንግስት ህዝቡን በማሳተፍ ተገቢውን የእርምት እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡

ሚያዝያ 7/2010/የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት/