ዜና ዜና

“የፍቅር እና የአንድነት ኪዳን” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ህዝባዊ መድረክ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በድምቀት ተካሄደ

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር፣ ክቡራን፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ክቡራን የኃይማኖት አባቶች፣ አባጋዳዎና ኡጋዞች፣ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችና አምባሳደሮች በተገኙበት በዚህ መድረክ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንደገለፁት ይህ ታላቅ ህዝባዊ መድረክ የተዘጋጀው፣ መንግሥት በአገራችን መጠነ ሰፊ የሪፎርም እርምጃዎችን ለማካሄድና የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የገባውን ቃል ለመፈጸም ይችል ዘንድ፣ ለለውጡ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን ብሄራዊ መግባባት ለማጎልበት ታስቦ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ዶክተር ነገሪ አክለውም ክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ፣ ከስህተታችን ተምረን፣ አገራችንን ለመካስ በርትተን በመስራት ውድ አገራችንን እናሳድግ ዘንድ በመካከላችን መተማመን፣ መተሳሰብ፣ ፍቅር፣ አንድነትና መደጋገፍ እንዲኖርና የስራ ወዳድነት ባህላችን እንዲጎለብት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየተዘዋወሩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እያካሄዱት ያለው የጋራ ግንኙነት አንዱ አካል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

መድረኩ፣ በአገራችን አስተማማኝ ሰላም፤ ዘላቂ ልማት፣ መሰረተ ሰፊ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በመንግሥት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከማገዝ አንጻር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበት መዘጋጀቱን ዶክተር ነገሪ ጠቅሰዋል፡፡

በንግግራቸው ማጠቃለያም በዚህ ታሪካዊና ታላቅ ህዝባዊ መድረክ ላይ ለተገኙ ታዳሚዎች በኢፌዴሪ መንግሥት ስም ምሥጋናቸውን አቅርበው፤ ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ላሉ፣ መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ መልዕክት እንዲያስተላልፉልን በታላቅ አክብሮት ጋብዘዋቸዋል፡፡

በድምሩ 25 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ፣ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተዉጣጡ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባለሃብቶች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት፣ የሚዲያ ተወካዮች፣ እና አርቲስቶች፣ እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተውበታል፡፡

የኢፌዴሪ የመ/ኮ/ጉ/ጽህፈት ቤት
ሚያዝያ 7 ቀን 2010 ዓ.ም.