ዜና ዜና

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የእንስሳት መድን ሽፋን መጀመሩ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ በሚያጋጥም የግጦሽ እጥረት ምክንያት በከብቶች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን የእንስሳት መድን ሽፋን መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ እንደተናገሩት፤ የእንስሳት መድን ሽፋኑ በክልሉ ከድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር የግጦሽ ሳር እጥረት ምክንያት በእንስሳቱ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ካሳ በመክፈል የአርብቶ አደሩን የችግር ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበርም ከመጋቢት 2010 ዓ.ም አንስቶ በአምስት ሺህ አባወራዎች ላይም በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል፡፡
ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚመራው የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መለሰ አወቀ በበኩላቸው፤ አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ በእንስሳት እርባታ ሥራ ላይ የተሰማራ አርብቶ አደር በመሆኑ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት የግጦሽ ሳር እጥረት በከብቶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ኑሮውን አስቸጋሪ እንዳደረገበት ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የእንስሳት መድን ሽፋኑ የሳተላይት የአየር መረጃን መሰረት በማድረግ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አርብቶ አደሩ ከብቶቹ ሞተውበት ችግር ውስጥ ከመግባቱ በፊት ሊደረስለት እንደሚገባ በማመን ወደዚህ ሥራ መገባቱን የጠቆሙት አቶ መለሰ፤ የሳተላይት የአየር ትንበያ መረጃን መሰረት በማድረግ ድርቅ ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው በተለዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ድርቁ ተከስቶ ከብቶቻቸው ከመሞታቸውና ችግር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ለመኖ መግዣ የሚሆን ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህም በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው የመድህን ሽፋን ቀደም ሲል ከነበሩት የመድን ዓይነቶች ችግሩ ከተከሰተና ጉዳት ከደረሰ በኋላ ከሚከፈል ካሳ የተለየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ካለፈው የመጋቢት ወር ጀምሮ በሙከራ ደረጃ ሲተገበር የቆየው የእንስሳት መድን ሽፋን መርሐ ግብር የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚመራው የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የመድን ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ከዛሬ ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ በይፋ ሥራ መጀመሩ ታውቋል፡፡

ሚያዚያ8/2010፤አዲስ ዘመን