ዜና ዜና

ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው ግብራቸውን መክፈል የሚያስችል አሰራር ተዘረጋ

ግብር ከፋዮች ባሉበት ቦታ ግብራቸውን መክፈል የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት መዘርጋቱን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር የግብር አከፋፈል ስርዓቱን ገቢራዊ አንደሚያደርገውም ገልጿል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ይህ 'ደራሽ' የተሰኘ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴ ግብር ከፋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢሌክትሮኒከስ መሳሪያዎች በሚጫን ሶፍትዌር ግብርን እንዲከፍሉ የሚያስችል ነው።

ባለስልጣኑ ከየካቲት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለተመረጡ አስር ከፍተኛ የግብር ከፋዮች ስለስርዓቱ ስልጠና መስጠቱን ጠቁመው፤ "ለቀጣይ ሁለት ወራት በሙከራ ደረጃ ተተግብሮ ውጤታማነቱ ይገመገማል" ብለዋል።

ስርዓቱ የግብር ከፋዩን ጊዜና ወጪን ከመቆጠቡም በላይ አላስፈላጊ የሆኑ የስራ ግንኙነቶችን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

የግብር ክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ሲሆን፤ ግብር ከፋዮች ከዚህ ቀደም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ አንደሚያገኙም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በአገሪቷ ያለውን የግብር አሰባሰብ ስርዓት ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ እየሰራ አንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል።

ሚያዚያ 5/2010 /ኢዜአ/