ዜና ዜና

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኃኪሞች አስመረቀ


የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለሁለተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 16 ሀኪሞች ሚያዝያ 6/2010 በዶክትሬት ዲግሪ አስመረቀ።

ምሩቃን በበኩላቸው በየትኛውም ጊዜና ቦታ ህብረተሰቡን በቅንነት፣ በታማኝነትና በርህራሄ ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡

ለምረቃ የበቁት ሀኪሞች ላለፉት 6 ዓመታት በኮሌጁ በንድፍ ሃሳብና በተግባር የተሰጠውን ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።

በምርቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ ሕክምና ከፍተኛ ማህበራዊ ኃላፊነት ያለበት ትልቅ ሙያ መሆኑን አስታውሰው፣ ምሩቃን በኮሌጁ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ሕብረተሰቡን ሳይሰለቹ ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

"ሙያው በየጊዜው ራስን ማሳደግና መማርን የሚጠይቅ ነው፤ በመሆኑም ይህን በመገንዘብ ሁልጊዜም ራስን በማብቃት የተሻለ ውጤታማ ሥራ ለመስራት መትጋት አለባችሁ" ብለዋል፡፡

ለተመራቂ ኃኪሞች ዲግሪና ክፍተኛ ውጤት ላመጡት የተዘጋጀውን ሽልማት የሰጡት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኢብራሂም ዑስማን ናቸው፡፡

ከንቲባ ኢብራሂም በእዚህ ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ያስመረቃቸው እጩ ሀኪሞች መንግስት በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት ለመፍታት እያደረጋቸው ላሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች አንድ ማሳያ ነው፡፡

የዕለቱ ምሩቃን ሀኪሞች ሕብረተሰቡን በታላቅ ሀገራዊና ሙያዊ ኃላፊነት በማገልገል በሀገር ደረጃ በጤናው ሴክተር እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ማስቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የዕለቱ ምሩቃን በበኩላቸው ህብረተሰቡን በየትኛውም ጊዜና ቦታ ያለምንም አድልኦ በቅንነት፣ በታማኝነትና በርህራሄ ቀን ከሌት ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡

ከምሩቃን መካከል በትምህርቱ 3 ነጥብ 6 በማምጣት ልዩ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ ዶክተር ራህመት በድሩ በበኩሉ "መነሻችንም መድረሻችንም ህብረተሰቡን በርህራሄና በቅንነት ማገልገል ነው፤ ይህንን ተልዕኮ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ" ብሏል፡፡

በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ዶክተር አለምፀሐይ ተሾመም በበኩሏ በቀጣይ በምትመደብበት ሥፍራ ሁሉ ጤናማና አምራች ሕብረተሰብ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደምተሰራ ተናግራለች፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአሁኖቹን ጨምሮ 60 ሀኪሞችን ማስመረቁ ታውቋል፡፡

ኢዜአ፣ ድሬዳዋ ሚያዚያ 6/2010