ዜና ዜና

የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ እየተደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ጥረት የሚያግዝ የአሥር ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ብአዴን ያበረከተውን የገንዘብ ድጋፍ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና አጠቃቀም ባለስልጣን ም/ኃላፊ ለአቶ በልስቲ ፈጠነ አስረከቡ፡፡

አቶ አለምነው የገንዘብ ድጋፉን አስመልክተው አቶ አለምነው ባደረጉት ገለጻ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀደም ሲል የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ምክር ቤት ባስቀመጧቸው አቅጣጫዎች ላይ የሁለት ቀን ውይይት ሲያደርግ ቆይቶ ብአዴን ህዝባዊነቱን እንደያዘ የቀጠለ ድርጅት ከመሆኑም በላይ ከህብረተሰቡ ጎን ቆሞ እንደሚታገል ለማረጋገጥ በተለይም ደግሞ በታላቁ የጣና ሀይቅና ወንዞች ላይ የተደቀነውን የእንቦጭ አረም ከአደጋ ለመታደግ በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተደረገ ያለውን ጥረት ማገዝ የሚያስችል ድጋፍ ማድረጉን አስገንዝበዋል፡፡

አያይዘውም እስካሁን በሐይቁ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ደለል በመቀነስ ዘርፈ ብዙ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፤ በጣና ሐይቅና አካባቢው ወንዞች ላይ የተከሰተውን መጤ አረም ለመከላከልም በትጋት እየተሠራ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ጣናን መታደግ ከጣና ራስጌ ያሉ እንደ መገጭ፣ ሰራባና ርብ ግድቦችን ከአደጋ መታደግ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን ለመፍጠር ዕድል እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ድጋፉ ከህዝቡ የተባበረ ጥረት ጋር ተዳምሮ መጤ አረሙን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማስወገድ ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና በቀጣይ ሐይቁን ለመታደግ ለሚደረገው ሁለንተናዊ ርብርብ ብአዴን ኢህአዴግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አሳስበዋል፡፡

በገንዘብ ርክክቡ ስነስርአት ወቅት የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና አጠቃቀም ባለስልጣን ም/ኃላፊ አቶ በልስቲ ፈጠነ በበኩላቸው ብአዴን ኢህአዴግ የእንቦጭ ማስወገድ ዘመቻን ለመደገፍ እየተደረገ ያለውን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ መሰረት አድርጎ በመወያየት ውሳኔ አሳልፎ የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረግ በመቻሉ ከፍተኛ ኩራት እንደተሰማቸው በመግለጽ ለድርጅቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም የተደረገው ድጋፍ የጣና ሐይቅን ከተጋረጠበት አደጋ ከመከላከል አንፃር ፋይዳው ትልቅ ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የጣና ሐይቅን ከመጤ አረምና ከሌሎች ተያያዥ ችግሮች ለማዳን እየተሠራ ያለው ሥራ ከዘመቻ ሥራ ወጥቶ የዘወትር ተግባር መሆን እንዳለበትና የሚመለከታቸው አካላት ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መረጃውን ያደረሰን የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ነው፡፡
ሚያዚያ 6/2010 ዓ.ም.