ዜና ዜና

ከውጭ ምንዛሪ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ እምነታችን ነው… ባለሀብቶችአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ መሰረታዊ እርምጃዎች እንደሚወስዱ እምነታቸው መሆኑን የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽንና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለባለሀብቱም ሆነ ለሕዝቡ መሰረታዊ ጉዳይ ለሆነው ሰላምና መረጋጋት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

ኢዜአ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በጤና፣ ትምህርት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶችንና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚያደርጉት ውይይት ምን እንደሚጠብቁ አነጋግሯል።

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር እንደተናገሩት፤ ለባለሃብቱ የሚያስፈልገው ዋነኛ ጉዳይ ሰላምና መረጋጋት ነው።

ኢንዱስትሪው ሰላማዊ እንዲሆን፣ የሰራተኛውና የአሰሪዎች መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ፣ ከሙስና የጸዳ አሰሪ እንዲፈጠር፣ ሙስናን የሚሞግት ትውልድ ለመፍጠርና የአገር ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም ጥያቄውን ለመፍታት የሚያስችል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ፍላጎታቸው እንደሆነ የተናገሩት አቶ ታደለ፤ በአገሪቷ አሁን የሚታየውን ሰላምና መረጋጋት ማስጠበቅና የባለሃብቱ ቁልፍ ጥያቄ የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ለባለሃብቱ መሰረታዊ የሆኑት የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የሰላም ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡ እምነታቸው መሆኑን በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች ተናገሩ።

በሆቴልና ቱሪዝም ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ታደሰ እያሱ እንዳሉት፤ የተሰማሩበት ዘርፍ በአገሪቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ከፍተኛ የሰው ሃይል በመቅጠር ቢታወቅም የውጭ ምንዛሬ በማጣት የሚፈለገውን አስተዋጽኦ እያበረከተ አይደለም።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሰጡ እምነታቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በምግብና መጠጥ ላይ የተጣለው የ15 በመቶ እሴት ታክስ ተገልጋዩ ላይ ቅሬታ እያስነሳ መሆኑን ጠቁመው፤ መፍትሄ እንዲሰጠው የቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ዳዊት ሞገስ እንዳሉት፤ ዘርፉ ለትርፍ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡን ለመርዳት የተቋቋመ እንደመሆኑ እንደሌሎች ድጋፍ እየተደረገለት አይደለም።

በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩት አብዱህማን ቁብሳ በበኩላቸው፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የትምህርት ፖሊሲው የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ለሟሟላት ባለሃብቱ ችግር እየገጠመው እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይ በሰው ሃይል ብቁ መምህራንን የሚያፈሩ ተቋማት እጥረት በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን የሚደረገው ከዩንቨርስቲ የሚመረቁ ልጆች እንደገና ለአንድ ዓመት እንዲሰለጥኑ ይደረጋል ይህ ደግሞ የጊዜና የገንዘብ ብክነት አለው፡፡

ባለሃብቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚች አገር ዕድገትና ለውጥ በሚያደርጉት መልካም ስራ ሁሉ ከጎናቸው በመሆን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሚያዚያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ከባለሃብቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ኢዜአ፣ አዲስ አበባ ሚያዚያ 6/2010