ዜና ዜና

በደቡብ ህዝቦች ክልል የበልግ ወቅት ዝናብ ለግብርናው ስራ አመቺ ነው - ሜቲዎሮሎጂበደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የበልግ ወቅት ዝናብ ለግብርናው ስራ እንቅስቃሴ አመቺ መሆኑን በብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የደቡብ አካባቢ ማዕከል ገለጸ፡፡

ወቅቱ ለክልሉ ደቡባዊና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የመጀመሪያው ዝናብ ወቅት ነው፡፡

በዚህ ወቅት ደቡብ ኦሞ ፣ ሰገን አካባቢ ህዝቦች፣ ጋሞ ጎፋ፣ ጌዴኦና ሲዳማ ዞኖች ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙ መሆናቸውን የማዕከሉ ትንበያና ትንተና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አንዱአለም ሽመልስ ተናግረዋል፡፡

"ሃዲያ፣ ከምባታ ሃላባ፣ጉራጌ፣ ስልጤና አጎራባች ዞኖች ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ዝናብ ያገኛሉ" ብለዋል፡፡

ከየካቲት 10 ጀምሮ የበልግ ወቅት ዝናብ መጀመሩን የገለጹት አስተባባሪው በክልሉ የዝናብ ማነስም ሆነ መብዛት በማንኛውም የግብርና እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አለማሳደሩን ገልጸዋል፡፡

ከህዳር እስከ የካቲት መግቢያ ዝናብ እንዳልነበረ አስታውሰው "የወቅቱ ዝናብ የአፈሩን እርጥበት በመመለስ የሰብሉንም ሆነ የግጦሽ ሳሩን የውሃ ፍላጎት እያሟላ ቆይቷል"ብለዋል፡፡

የወቅቱ ሁለት ወራት የተጋመሱ ሲሆን በተለይ በማሳ ዝግጅት በዘር መብቀልና በኩትኳቶ ደረጃ ላለ ሰብል አመቺ እና ዝናቡ ተስማሚ መሆኑን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ በቀጣይ የሚኖረው የአየር ሁኔታ ትንበያ እንደሚያሳየው ሁሉንም የክልሉን አካባቢዎች ያማከለ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች እንቅስቃሴያቸውን ይህንን ተከትለው በቅርበት ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከክልሉ አደጋ መከላከል እንዲሁም ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ጋር የቅርብ መረጃ ልውውጥ ስለሚደረግ በዚህ እንዲጠቀሙና በቅርበት የሚደረግላቸቸውን የግብርና ባለሙያ ድጋፍ እንዲከታተሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ኢዜአ/ሀዋሳ ሚያዝያ 4/2010