ዜና ዜና

ኢትዮጵያና ብራዚል በኢንቨስትመንት መስክ አብሮ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

 

 

 

 

 

 

 

ኢትዮጵያና ብራዚል በኢንቨስትመንት መስክ አብሮ መስራት የሚያስችላቸው ስምምነት በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።

ስምነቱን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እና የብራዚሉ አቻቸው አምባሳደር ፈርናንዶ ሆዜ ማሮኒ ተፈራርመዋል።

የዛሬው ስምምነት በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮጵያና ብራዚል የመጀመሪያው የሁለትዮሽ የምክክር መድረክ ላይ የተፈረመ ነው።

ወይዘሮ ሂሩት በምክክር መድረኩ ኢትዮጵያ እና ብራዚል በኢንቨስትመንት እና በንግድ ዘርፎች ያላቸው ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር አለበት ብለዋል።

አክለውም የብራዚል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተሳታፊ ቢሆኑ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

የተፈረመው ስምምነትም ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚያበረታታና በሁለቱ ሀገራት መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲካሄድ ይረዳልም ነው ያሉት።

የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ፈርናንዶ ሆዜ ማሮኒ በበኩላቸው፥ ሃገራቸው የተለያዩ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ እንደምታበረታታ ተናግረዋል።

የሁለቱን ሃገራት የሁለትዮሽ ትብብር፣ በኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ትምህርት ዘርፎች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።

በዛሬው ውይይት ላይ የብራዚል የዲፕሎማቲክ አካዳሚ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ፍላጎት መግለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሚያዚያ 3፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)