ዜና ዜና

የገለልተኛ ንቅናቄ አባል አገራት ስብሰባ በባኩ ተካሄደ፡፡


በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሂሩት ዘመነ በአዛርባጃን ባኩ ከተማ በተካሄደው የገለልተኛ አገሮች ንቅናቄ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ግጭትን ለማስወገድ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስብሰባው ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ የአፍሪካ ቡድንን ወክለው ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካ ለገለልተኛ ንቅናቄ እሴቶችና መርሆች መከበር ቁርጠኛ ነው። ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና በሰለጠነ መንገድ ክርክር ለማድረግ አፍሪካ አበክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡

ግጭትን መከላከል እና የድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ ላይ በሚገባ ለመስራት የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ከስብሰባው ጎን ለጎን ወ/ሮ ሂሩት ዘመነ ከጅቡቲ አቻቸው ሞሃመድ አሊ ሀሰን እና ከሱዳን አቻቸው አምባሳደር ሞሃመድ አብደላ ኢድሪስ ጋር በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ በአዛርባጃን የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ ከሆኑት ሴሪሁን አላክባሮቭ የሁለቱ አገራትን ግንኙነት ሊያጠናክሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በክብር ቆንስላው አስተባባሪነት የአዘርባጃን የቢዝነስ ቡድን በመጭው ወራት ኢትዮጵያን ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።

መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ነው፡፡

ሚያዝያ፣ 2/2010