ዜና ዜና

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የቆየው የሶስትዮሽ ውይይት ተጠናቀቀ

በሱዳን ካርቱም ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የሶስትዮሽ ውይይት ተጠናቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደገለፁት፥ ስብሰባው በግልጽነትና በመተማመን መንፈስ የተካሄደ ነው።

በዚህ ውይይት ላይ የውሃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎችንም ተሳትፈዋል።

የሶስቱ ሀገራት ሚኒስትሮች በህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቅ በተመለከተ የተወያዩ ሲሆን፥ በሌሎች አበይት የሶስትዮሽ ጉዳዮች ላይም መክራዋል ነው የተባለው።

በዚህም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙርያ በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ከመግባባት መድረሳቸውን የተናገሩ ቃል አቀባዩ፥ በቀጣይ ባልተቋጩ ጉዳዮች ዙርያ ለመወያየት መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

በባለፈው ጥር 21 2010 ዓ.ም መሰረተ ልማት ፈንድ በማቋቋም ሶስቱ ሀገራት በመሰረተ ልማት እንዲተሳሰሩ ለማድረግ በመሪዎች ደረጃ የተሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።

መጋቢት 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)