ዜና ዜና

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

የህዳሴው ችቦ በተዘዋወረባቸው በዞኑ 14 ወረዳዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች አንድ ሚሊዮን 800ሺህ ብር በቦንድ ግዥ ተሰብስቧል፡፡

በዞኑ ወገራ ወረዳ የኖራ ጻድቃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላት ታከለ በሰጡት አስተያየት " ከዚህ ቀደም በግሌ የ300 ብር ቦንድ ገዝቻለሁ፤ ዘንድሮም የህዳሴው ችቦ ወደ አካባቢው መምጣቱን በማስመልከት የ100 ብር ቦንድ ግጭ ፈፅሚያለሁ" ብለዋል ።

አርሶ አደሩ ለኢዜአ እንዳሉት እርሳቸውን ጨምሮ የቀበሌው አርሶ አደሮች በጋራ በመሆን ከ60 ሺህ ብር በላይ በስጦታ አበርክተዋል ።

የጣቁሳ ወረዳ ነዋሪ ቄስ አዳና ማህተም በበኩላቸው ቀደም ሲል ከገዙት የ3ሺህ ብር ቦንድ በተጨማሪ ዘንድሮ የግድቡ ግንባታ መሰረት የተጣለበትን ሰባተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የ1ሺህ ብር ቦንድ ለመግዛት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።

"እስካሁን ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል የ400 ብር ቦንድ ገዝቻለሁ" ያሉት ደግሞ የጭልጋ ወረዳ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ኮኬ ናቸው፡፡

የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን ሰባተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የአካባቢውን አርሶ አደሮችን በማንቀሳቀስ ቦንድ ለመግዛት ማሰባቸውን ገልፀዋል።

የግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ያመለከቱት፡፡

የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አማረ በበኩላቸው በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም የህዳሴው ችቦ በተዘዋወረባቸው 14 ወረዳዎች የሚገኙ አርሶአደሮችና ሌሎች ነዋሪዎች የአንድ ሚሊዮን 800ሺህ ብር የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡

"የግድቡ ግንባታ መሰረት የተጣለበት ሰባተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በቦንድ ግዥ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል " ብለዋል፡፡

በዓሉን በቦንድ ሽያጭ፣ ድጋፉን ለማጠናከር በሚያግዙ ህዝባዊ ውይይቶችና በኪነጥበብ ዝግጅቶች ለማክበር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እሰካሁን የዞኑ ህዝብ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ128 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል ።

መጋቢት 17/ 2010 / ኢዜአ /