ዜና ዜና

ህዝቡ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ህዝቡ ለታላቁ ኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሻራውን ለማኖር እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ጥሪ አቀረቡ።

የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 7ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ ትናንት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የትያትርና ሙዚቃ ጥበባት ትምህርት ‘‘የአባይ ዘመን‘‘ በሚል ርእስ የተዘጋጀ ድራማዊ ሙዚቃ ለእይታ ቀርቧል።

ወይዘሮ ሮማን በዚሁ ወቅቱ እንደገለፁት የህዳሴ ግድብ የኢትዮጰያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተስማምተው እየገነቡት ያለ ግዙፍ ፕሮጀክታቸው ነው።

"በየደረጃው የሚገኘው ህዝብ ከድህነት ለመላቀቅ እየገነባው ላለው ግድብ እስካሁን ያደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ነው"ብለዋል።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከማህበራት፣ ከባለሃብቶች፣ በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ጨምሮ ከመላው የኢትዮጰያ ህዝብ በቦንድ ግዢና በስጦታ እስካሁን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል ።

"ከዚሁ ጎን ለጎን ወደ ግድቡ የሚገባውን ደላል አስቀድሞ ለመከላከል በአርሶ አደሮች 79 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል" ብለዋል ።

በሃገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በምርምርና ጥናት ስራዎች፣ በውጭ የዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ድጋፍ ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ህጻናት ሳይቀሩ ከቤተሰቦቻቸው ለከረሜላ መግዣ ከሚሰጣቸው ሳንቲም በመቆጠብና በማሰባሰብ ድጋፍ አድርገዋል" ያሉት ወይዘሮ ሮማን ግድቡ ኢትዮጰያዊያን ድህነትን ለማጥፋት ተስማምተው እየገነቡት ያለ የአንድንታቸው መገለጫ አርማ መሆኑን ገልፀዋል ።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የግድቡን ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ ውድ ዋጋ ላለው ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በየደረጃው የሚገኘው ህዝብ በግድቡ ግንባታ አሻራውን ለማኖር እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ወይዘሮ ሮማን ጥሪ አቅርበዋል ።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ ከገንዘብ በተጨማሪ የተለያዩ የምርምርና ጥናት ስራዎችን በማካሄድ ግንባታው በማህበራዊ ፣ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መስኮች ባለው ገፅታ ላይ ትንታኔዎችን ሲያቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል ።

በቀጣይም ዩኒቨርሲው የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል ።

በግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ የትግራይ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ሃይለኪሮስ ሳህለ በበኩላቸው ለግድቡ ግንባታ በክልሉ እስካሁን በገንዘብና አርሶ አደሩ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በዚህ አመት የህዳሴ ግድቡ ዋንጫ በክልሉ በተዘዋዋረበት አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ መሰረት ድንጋይ የተጣለበት 7ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ትናንት በመቀሌ ከተማ የሰማእታት ሓውልት መሰብሰቢያ አደራሽ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የትያትርና ሙዚቃ ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀ ‘የአባይ ዘመን‘‘ የተሰኘ ድራማዊ ሙዚቃ ለእይታ ቀርቧል።

ሙዚቃዊ ድራማው የኢትዮጰያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና የአኗኗር ዘቤ ቢኖራቸውም በግድቡ ግንባታ ላይ የጋራ ፍላጎትና መነሳሳት እንዳላቸው የተንጸባረቀበት መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ኢትዮጰያዊያን እስካሁን ለግድቡ ግንባታ ያደረጉትን ድጋፍና የፈጠሩት አንድነት እንዲሁም የግድቡ ግንባታ እስከ ፍጻሜው ለማድረስ እጅ ለእጅ ተያይዘው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ያሳየ መሆኑ ተመልከቷል።

ድራማዊ ሙዚቃው ለእይታ በቀረበበት መድረክ ላይ የሃገር መከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላት፣ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የስራ ኃላፊዎችና ማህበረሰብ፣ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

መጋቢት 17/2010 / ኢዜአ /