ዜና ዜና

የቆቃ-አዱላላ-ቢሾፍቱ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ነው

በኦሮሚያ ክልል የቆቃ-አዱላላ-ቢሾፍቱ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ
ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ነው ተባለ።

52 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና 711 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የቆቃ- አዱላላ -ቢሾፍቱ የመንገድ ፕሮጀክት በየካቲት 2007 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁን በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ገልጸዋል፡፡

ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነው ይህ መንገድ ካለው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ አንፃር በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ግንባታው የተከናወነ ነውም ተብሏል፡፡

ዳይሬክተሩ ስለ መንገዱ ጠቀሜታ ሲናገሩ የአካባቢው ህብረተሰብ የተሻለና ዘመናዊ የመንገድ ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በመስመሩ አበባ ምርትን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎች በብዛት የሚመረትበት አካባቢ በመሆኑ ምርቱን በቀላሉ ወደ ገበያ ማዕከላት ለማድረስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በአካባቢው ላይ በርካታ ማዕድናት ለሲሚንቶ ምርት ግብአት የሚሆኑ እንደ ኖራ ድንጋይና ሌሎችም ግብዓቶች ወደ ፋብሪካ በቀላሉ እንዲደርሱ የመንገዱ መሰራት ጥቅም አለው።

ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚውሉ አሽዋ በብዛት የሚገኝበት አካባቢ በመሆኑ ወደ ተለያዩ ግንባታዎች ለማድረስ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ግንባታውን አሰር የተባለ ሀገር በቀል የኮንስትራክሽን ድርጅትእና የመንገዱን ጥራት ኔት ኮንሰልታንት የተባለ ሀገር በቀል አማካሪ ድርጅት አከናውናውታል፡፡

መስመሩ ዝቋላ አቦ የሚገኝበት መስመር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምዕመናን ወደ ስፍራው ለሚያደርጉት ጉዞ አመች ያደርግላቸዋልም ተብሏል።

በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችና ተጠቃሚ አሽከርካሪዎች ለመንገዱ ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርጉለት እንደሚገባ አቶ ሳምሶን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአሰር ኮንስትራክሽን የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አይናለም ፍቃዱ በበኩላቸው
መንገዱ ከተማ ማዕከል በመሆኑ 3 ከተሞችን ያገናኛል። ስለዚህ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በኔት ኮንሰልት አማካሪ መሃንዲሶችና አርክቲክቸሮች የግል ማህበር ተጠሪ መሃንዲስ የሆኑት አቶ ባረከ በለው እንዳሉት መንገዱ ደረጃውን በጠበቀና በጥራት ጊዜውን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንና በተጠበቀው መንገድም መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በመንገዱ በተደጋጋሚ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በነበረው መንገድ ሲጠቀሙ የጊዜ ብክነትና የተሸከርካሪ ጉዳት ያጋጥማቸው የነበረ ሲሆን አሁን ግን መንገዱ አስፓልት መሆኑ ችግሩን እንደቀረፈላቸው ተናግረዋል፡፡

መጋቢት 3/2010/የኢፌዴሪ መ/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት