ዜና ዜና

በደቡብ ህዝቦች ክልል ለልማት እቅዶችና ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናታዊ መረጃዎች ተዘጋጁ

ከህብረተሰቡ ኑሮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማካተት ለልማት እቅዶችና ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናታዊ መረጃዎች ማዘጋጀቱን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሀዝቦች ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጃቸው እነዚህን  ጥናታዊ መረጃዎች የሚያስተዋውቅ  የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ የቢሮ ኃላፊው አቶ ታምራት ዲላ እንደገለጹት ጥናታዊ መረጃዎቹ  የህብረተሰቡ ኑሮ ያለበትን ነበራዊ ሁኔታ በትክክል የሚያሳይ  ነው፡፡

ክልሉ ያካሄደው ይሄው ጥናት ለልማት እቅዶችና ለፖሊሲ ዝግጅት የሚሆን ከህብረተሰቡ ኑሮ ጋር የተያያዙ ዋና ዋና መረጃዎችን በአንድ ሰነድ የያዘ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ ታምራት እንዳመለከቱት ጥናታዊ መረጃዎቹ ታትመው ስራ ላይ ሲውል መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ መስሪያ ቤቶች ለሚታቀዱ እቅዶች መነሻ ከመሆን ባለፈ የስነ ህዝብ ጉዳዮችን በልማት እቅዶች ውስጥ አካቶ ለመተግባር ጠቃሚ ይሆናል፡፡

በቢሮው የስነ ህዝብ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ በበኩላቸው "በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥር ከኢኮኖሚው ጋር አለመመጣጠኑ ለጥናቱ መነሻ ነው" ብለዋል፡፡

የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የአስር ዓመታት መረጃዎች ተሰብስቦ ነባራዊ ሁኔታውን መሰረት አድርጎ የተካሄደ ጥናት መሆኑንም  አመለክተዋል፡፡

"የተለያዩ የልማት አመላካቾች ከስነ ህዝብ ጉዳዮች ጋር ያላቸውን መስተጋብር ሳይንሳዊ በሆነ ሁኔታ በመተንተን የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እቅዶችና ፕሮግራሞች እንዲነደፉ ያግዛልም" ብለዋል፡፡

ጥናቱ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ህዝብ ፈንድ በተገኘ ድጋፍ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተሰራ ነው ተብሏል፡፡

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰርና የጥናቱ አስተባባሪ ዶክተር ዳንኤል  በኃይሉ እንዳሉት ጥናቱ የሕዝቡን ለውጥ በእድሜና ጾታ፣የጤና፣ የስነ ጾታና የአካባቢ እድገትን ከህዝቡ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር የተሰራ ነው፡፡

አንድ ዓመት ተኩል በፈጀው በዚህ ጥናት ከ20 ሴክተር መስሪያ ቤቶች መረጃ የተሰበሰበ ሲሆን 147 ዓይነት መለኪያዎችን መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡

"በአለም ላይ የስነ ህዝብ ሁኔታዎች ትንተናን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ያጠኑ ሃገራት ጥቂት ናቸው" ያሉት ዶክተር ዳንኤል በአፍሪካ በኬንያ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱንና ልምዳቸውን መውሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሕዝቡን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ያደረገ ሳይንሳዊ ጥናት በመሆኑ መንግስት ለሚያወጣቸው እቅዶችም ሆነ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አፈጻጸም ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሃም አላሮ በበኩላቸው  የጤናው ዘርፍ ከየትኛውም ሴክተር በበለጠ የስነ ህዝብ መረጃዎች ጋር ተያይዞ ስለሚሰራ  ጥናቱ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

"ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መረጃዎች በአንድ ሰነድ ተጠናክረው መቀመጣቸው ሃሰተኛ ሪፖርቶችን ከማስቀረት ባለፈ የጤና መረጃን በተገቢው ለማድረስ የሚያግዝ ነው "ብለዋል፡፡

በመድረኩ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ሀዋሳ መጋቢት 3/2010