ዜና ዜና

የኢፌዴሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ከፊንላንድ የውጭ ንግድና ልማት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል ከፊንላንድ የውጭ ንግድና ልማት ሚኒስትር አኔ ማሪ ቪሮሊኔን ጋር ተወያዩ።

ሚኒስትር ዲኤታው በዚህ ወቅት ኢትዮጵያና ፊንላንድ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው፥ ሃገራቱ ግንኙነታቸውን በንግድ እና ኢንቨስመንት ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የፊንላንድ መንግስት በግብርና ዘርፍ በኢትዮጵያ ለሚያደርገው የልማት ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የፊንላንድ ባለሃብቶችም በሃገሪቱ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አውድ በመጠቀም መዋዕለ ነዋያቸውን ቢያፈሱ ውጤታም ይሆናሉ ብለዋል።

የፊንላንድ የውጭ ንግድና ልማት ሚኒስትር አኔ ማሪ ቪሮሊኔን በበኩላቸው፥ የሁለቱን ሃገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለልማትና ዴሞክራሲ ዕድገት የምታደርገውን ጥረትም ፊንላንድ እንደምትደግፍ ጠቅሰዋል።

የፊንላንድ ባለሃብቶችም በግብርና፣ በትምህርት፣ በንፅህና ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘርፎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል።

መጋቢት 3 ፣ 2010/ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት