ዜና ዜና

የእንቦጭ አረምን በዘመናዊ ማሽን የማስወገድ ስራ ተጀመረ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በጣና ሀይቅ ላይ የተዛመተውን የእንቦጭ አረም በዘመናዊ ማሽን የማስወገድ ስራ ተጀመረ።

የእንቦጭ አረምን የማስወገድ ስራው የተጀመረው በባህር ዳር የተቋቋመው አማጋ የስፖንጅ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት ገዝቶ ለክልሉ ባስረከበው በዘመናዊ ማሽን መሆኑን የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

ድርጅቱ ገዝቶ ልክልሉ መንግስት ያስረከበው ዘመናዊ ማሽንም በሰዓት 5ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚገኝ የእንቦጭ አረምን የማስወገድ አቅም ያለው መሆኑ ከዚህ ቀደም መነገሩ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ለእምቦጭ ማስወገጃ ያመጣውን ዘመናዊ ማሽን ኦፕሬተሮችን ሙሉ ወጪ በመሸፋን ከውጭ ሃገር ባለሙያ አስመጥቶ ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።

ስልጠናው እየተከናወነ ያለው ማሽኑ በሚገኝበት ጎርጎራ ወደብ አካባቢ ሲሆን፥ ከ40 በላይ በቴክኒክና ሙያ የተመረቁ የአካባቢው ወጣቶችና የጣና ሀይቅ ድርጅት የቴክኒክ ሰራተኞች መሆናቸውም ተነግሯል።

በጣና ሀይቅ ላይ የተዛመተው የእንቦጭ አረም የፊውን የሃይቁን ክፍልና ገዳማቱን ያካለለ ሲሆን፥ ይህንን አረም ለማስወገድ ጣና አሁን ባለበት ደረጃ ከሰባት በላይ ተመሳሳይ ዘመናዊ ማሽኖች እንደሚያስፈልጉት ባለሙያወች ይናገራሉ።

ስለሆነም ጣናን ለመታደግ በሚደረገው ማንኛውም ስራ ላይ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉም ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)