ዜና ዜና

“የዜጎችን በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነት መብቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትን መወጣት ለዘላቂ ሰላም አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው” - የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

 

 

 

 

 

 

 

 

የዜጎችን በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነት መብቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት መወጣት ዘላቂ ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ክቡር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ገለጹ።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከተካተቱት ጠቅላላ ድንጋጌዎች አንድ ሦስተኛ ያህሉ የሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ነገሪ ከተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች መካከልም አንዱ፣ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በህይወት የመኖር እና የአካል ደህንነት መብት ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል። እነዚህን መብቶች በማክበርና በማስከበር ረገድ ህገመንግሥቱ ከፍተኛውን ኃላፊነት የጣለው በዋነኝነት በመንግሥት ላይ መሆኑም ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታትና የህዝቦቻችንን ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ቀይሶ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ አልፎ አልፎ በዜጎቻችን ህይወትና ንብረቶች ላይ ጉዳት ሲደርስ እንደሚስተዋል የገለጹት ዶክተር ነገሪ፦ "ይህ ሁኔታ፣ ህዝባችን በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ የሚሸረሽር ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ የአገራችንን ገጽታ እየጎዳው መሆኑን" ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ በትናንትናው እለት በኦሮሚያ ክልል፣ በቦረና ዞን፣ በሞያሌ በሰላማዊ ዜጎቻችን ላይ የደረሰዉ የሞትና የመቁሰል አደጋ አስመልክተው ሲናገሩም ፦ "በየትኛውም መስፈርት ቢሆን ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ፣ ጥፋቱን በፈፀሙት ላይ አስተማሪ ሊሆን የሚችል ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በኮማንድፖስቱ እንደተገለፀዉ መንግሥት ከህዝቡ ጋር ሆኖ እንደሚሰራ እያረጋገጥን ህይወታቸውን ላጡ እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በራሴ እና በኢፌዴሪ መንግሥት ስም ለመግለጽ እወዳለሁ " ብለዋል።

"ውድ የሆነው እና ፍጹም መተኪያ የሌለው የሰው ህይወት ከጠፋ በኋላ እንደገና መመለስ የማይችል እንደመሆኑ መጠን፣ በዜጎቻችን ላይ ይህን መሰሉ ስህተት ዳግም እንዳይፈፀም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸው መሆኑን መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ ይወዳል" ሲሉም አክለው ገልጸዋል፡፡

መጋቢት 2/2010/የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት