ዜና ዜና

ሰላምና አንድነታችንን ጠብቀን ለግድቡ እውን መሆን የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን- የህዳሴው ግድብ አምባሳደር

ሰላምና አንድነታችንን ጠብቀን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ስትል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አምባሳደር ወይዘሪት ሩታ አያሌው ተናገረች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአምባሳደርነት ውድድር ተካሄዷል።

በውድድሩ ዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችን የወከሉ እንስቶች ተሳታፊ ነበሩ።

እያንዳንዱ ክልልና የከተማ አስተዳደር ከዚህ በፊት ባካሄዱት ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ ወይዛዝርት በውድድሩ የተካፈሉ ሲሆን፤ አማራ ክልልን የወከለችው ሩታ አያሌው ውድድሩን በማሸነፍ የግደቡ አምባሳደር ሆናለች።

ሩታ አያሌው ውድድሩን በማሸነፏ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል እንደምትሆንም ተገልጿል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ  ታገል ቀኑብህ እንዳሉት፤ የውድድሩ ዋና ዓላማ ሴቶች በግድቡ ላይ ያላቸውን ሚና ይበልጥ ማጎልበት ነው።

"ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሰፊ ቅስቀሳና መረጃ አንዲሰጡ ለማድረግና በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለህበረተሰቡ እንዲሰጡ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው።"ብለዋል፡፡

"በግድቡ ዙሪያ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ቆንጆ ናቸው" ያሉት አቶ ታገል፤ በዚህ ምክንያት ውድድሩ የቁንጅና ከሚለው ይልቅ 'የታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አምባሳደርነት ውድድር' የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ጠቁመዋል።

"ውድድሩ ሴቶች ያላቸውን ተፈጥሯዊ ክህሎት ተጠቅመው የግድቡን ሁለንተናዊ ፋይዳ አንዲያስተዋውቁ ይረዳል" ያሉት ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ገዛኸኝ አባተ ናቸው።

የውድድሩ አሸናፊ ወጣት ሩታ አያሌው በበኩሏ ኢትዮጵያዊያን ከሶስት ሺህ ዘመን በላይ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አውስታ፤ "አንድነታችንን በመጠበቅ ግድቡን እንጨርሳልን" ስትል ለግድቡ እውን መሆን ያላትን እምነት ገልጻለች።

ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋርም ሆነ በተናጥል በምታደርገው እንቅስቃሴ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ እንደምታስተዋውቅም ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በውድድሩ አንደኛ ለወጣችው የ35 ሺህ ብር ቦንድ ያበረከተ ሲሆን፤ ሁለተኛና ሶስተኛ ለወጡት እንደ ቅደም ተከተላቸው የ25 ሺህ እና 15 ሺህ ብር ቦንድ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

መጋቢት 2/2010፤ኢዜአ