ዜና ዜና

በሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉብኝት ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት አስመዝግባበታለች

የአሜሪካ፣ የሩሲያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሳምንቱ ባደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ማስመዝገቧን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ገለፁ።

ዶ/ር ወርቅነህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን ጉብኝት አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ "ሳምንቱ ታሪካዊና ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሳምንት ተደርጎ የሚወሰድ ነው" ብለዋል።

የሚኒስትሩቹ ጉብኝት አገራቱ ከኢትዮጵያ ባላቸው የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከርና ቀደም ብሎ የተያዘ እንጂ ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ የማይያያዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጉዳይ በታሪካችንም የኢትዮጵያውያን እንጂ የሌላ አካል አለመሆኑን የገለፁት ዶ/ር ወርቅነህ አገራቱ ይህንም እንደተረዱትና እንደሚያከብሩት ተናግረዋል።

ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ፣ በእፍሪካ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ በሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ዲፕሎማሲ መስክ ላላት አስተዋፅኦ በድጋሚ የተሰጠ እውቅና ነውም ብለዋል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴለርሰን የተደረገው ጉብኝትም አገሪቱ ለኢትዮጵያ ያላትን ወዳጅነትና ዴሞክራሲያ ሽግግር አጋርነቷን ያሳየችበት እንደሆነ ዶ/ር ወርቅነህ ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ዶ/ር ወርቅነህ ትብብሩን በተለይ በኢኮኖሚው መስክ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር የተደረገው ውይይትም ሁለቱ አገራት ላለፉት 120 ዓመታት የገነቡትን ግንኙነት የበለጣ ማጠናከር በሚቻልባችው ጉዳዮች ዙሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት በርእዮተ ዓለም የተቃኘ ሳይሆን ለአገራቱ ህዝቦች የጋራ ጥቅም በሚውሉ ተግባራዊ የልማትና የኢኮኖሚ አጀንዳዎች ላይ ነው ብለዋል።

የሁለቱን አገራት ግንኙነት በኢኮኖሚ ፣ በንግድ ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢነርጂ ዘርፎች ይበልጥ ለማሳደግ መስማማታቸውንም ዶ/ር ወርቅነህ ተናግረዋል።

ዶ/ር ወርቅነህ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልክቶ ሲናገሩ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ስምምነት ለመፈራረም፣ የተወሰኑ የህግ አንቀጾችን የማጣጣም ስራዎች ብቻ መቅረታቸውን፣ ዜጎቻችን በአረብ ኤምሬቶች ክብራቸው ተጠብቆ፤ መብታቸው ሳይደፈር መስራት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር መስማማታቸውን ተናግረዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱን ለማጠናከር መስማማታቸውንና እስካሁን 10 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ 98 ያክል የአገሪቱ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እየሰሩ ነው።

የካቲት30/2010/የው/ጉ ዳይ ሚንስቴር