ዜና ዜና

አሜሪካ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ሂደት እንደምትደግፍ አስታወቀች

በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ሬክስ ቴሌርሰን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የዴሞክራሲ ግንባታና የኢኮኖሚ ለውጥ አገራቸው እንደምትደግፍ እስታውቀዋል።

አገራቸው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እንደምትከታተል ገልፀው የዲሞክራሲ ሂደት እንዲጎለብት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደትና ሽግግር የሌላ አገር ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ውሳኔ ብቻ እንደሆነም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ በአገሪቱ እየተስተዋለ ላለው የፀጥታ መደፍረስ መፍትሔው ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያውያንም መንግስት የጀመረው ለውጥ እንዲደግፉና ከሁከት በመታቀብ ለለውጡ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ መወሰናቸው ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች አገራትም በምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ጠቃሚና ጠንካራ አጋራችን ነች፤ አሁን በምታደርገው ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደትም ገንቢ ድጋፍ እናደርጋለን" ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ለአፍሪካ ቀንድ ብሎ ለአህጉሩ ዘላቂ ሰለምና መረጋጋት የኢትዮጵያ ጠንካራ ሆኖ መውጣት ወሳኝ መሆኑን ገልፀው አሁን ተግባራዊ እየሆነ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጭር እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበርና አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ አገራት ስደተኞችን ተቀበላ በማስተናገዷ አሜሪካ ታደንቃለች ብለዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የተሻገረ የማይዋዥቅ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑንና በዚህም ኢትዮጵያ ደስተኛ መሆኗን ተናግረዋል።

በዴሞክራሲ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልማት መስኮች አሜሪካ እስካሁን ለኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍና አውነተኛ አጋርነት አመስግነዋል።

ዶ/ር ወርቅነህ እንዳሉት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እያደረገች ባለችበት ወቅት እየተከናወነ ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲሌርስን ጉብኝት አሜሪካ የኢትዮጵያ ትክክለኛ ወዳጅ መሆኗን የሚያሳይ ነወ።

የአገራቱ በፖለቲካና ፀጥታ ጉዳዮች ያላቸው ጠንካራ ትብብር በንግድና ኢኮኖሚም ዘርፍም ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀው ለዚህም ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባላት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች የአሜሪካ ባለሃብቶች መጥተው እንዲሰማሩ ጥሪ ያቀረቡት ዶ/ር ወርቅነህ መንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት በተለይም በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ሁለቱ አገራት ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ አስረድተዋል።

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በመከባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉም ሬክስ ቲለርሰን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት የምታደረግውን ጥረት አሜሪካ እንደምታደንቅ ገልፀው አገራቱ ከፖለቲካ ባሻገር የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸው እንዲጎለብት አሜሪካ ዝግጁ ነች ብለዋል በማለት መረጃውን ያደረሰን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት ነው፡፡

የካቲት, 30/2010