ዜና ዜና

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሰባተኛ ዓመት በአማራ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገለጸ

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት ሰባተኛ ዓመት በአማራ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የክልሉ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ላቀ ጥላዬ እንዳሉት በዓሉን ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ከመጋቢት 1 እስከ መጋቢት 24/2010ዓ.ም ድረስ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል፡፡

የፓናል ውይይት፣ የስነ-ፅሁፍ ምሽት፣ የጥያቄና መልስ ውድድር፣ የቲያትርና የሙዚቃ ኮንሰርት ለበዓሉ ከተዘጋጁት መካከል ይገኙበታል፡፡

ህብረተሰቡ የቁጠባ ባህሉን እንዲያሳድግና ለህዳሴው ግድብ የሚያደርገውን የቦንድ ግዥ ተሳትፎ አጠናክሮ በሚቀጥልበት መልኩ በዓሉ ይከበራል፡፡

የህዳሴው ችቦ ከጥር 1/2010ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ለአንድ ወር ያህል በ11 ዞኖችና በሶስት ሜትሮ ፖሊታን ከተሞች ሲዘዋወር በቆየባቸው ጊዜያት ከተለያዩ የህብረተስብ ክፍሎች ፣ ተቋማትና ማህበራት 15 ሚሊዮን 800ሺህ ብር በቦንድ ግዥ መሰብሰቡን ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ወቅት በየአካባቢው የተሰየሙ የህዳሴው ግድብ ቋሚ አደባባዮች በቀጣይ የህዳሴው ግድብ የሚያስገኘውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አጉልተው በሚያሳይ መልኩ እንደሚገነቡም ጠቁመዋል፡፡

ግድቡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድ ያስተሳሰረ በመሆኑ በዓሉን የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዥ በንቃት በመሳተፍ እንዲያከብረውም ጥሪ አቅርበዋል።

በቀረጢትና ዱቄት ማምረት ስራ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ባይህ መኮነን በሰጡት አስተያየት የህዳሴው ችቦ ባህርዳር በቆየበት ወቅት የ50 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁንም የ550 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ ማከናወናቸውን አስታውሰው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ደሳለኝ እውነት በበኩሉ የህዳሴው ችቦ በተዘዋወረበት ወቅት በግድቡ ላይ አሻራውን ለማስቀመጥ የ65 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ ለመጀመሪያ ጊዜ መፈፀሙን ተናግሯል።

በአማራ ክልል በተያዘው ዓመት ለማሰባሰብ ከታቀደው 100 ሚሊዮን ብር ውስጥ እስከ ጥር 30/2010ዓ.ም ድረስ 78 በመቶው መከናወኑ ተመልክቷል፡፡

የካቲት 29/2010 /ኢዜአ/